ምክር ቤቱ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ።

61

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡

በምክር ቤቱ የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ.ር) ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሰጣቸው ተቋማዊና አሥተዳደራዊ ነጻነት በመጠቀም በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት የሚያከናውኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ አዋጁ በሀገሪቱ የተጀመረውን የትምህርት ጥራት ሪፎርም የሚያጠናክር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከተለመደው የቢሮክራሲ አሠራር በመውጣት ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲሠሩ የሚያስችላቸው አዋጅ እንደኾነም ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ.ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጡና የሚጠኑት ጥናቶችም ችግር ፈቺ እንዲሆኑ የሚያግዝ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡

አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎች ጫና እንዳይኖርባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ.ር) ጠቁመው፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወደ ራስ ገዝነት ለማብቃት እየተሠራ መኾኑንና በሂደት ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ራስ ገዝ ለመኾን የሚያስችላቸውን መስፈርት እንዲያሟሉና እንዲወዳደሩ ያስችላል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲያጎለብቱ የሚያስችል መኾኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸው ነገር ግን የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የፕሬዚዳንቶች ሹመት፣ የኦዲት ሥርዓት እንዲሁም ሁሉንም ማኅበረሰብ አካታች እንዲኾኑ ማድረግ የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎች ሊዘጋጁ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በአራት ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ ተአቅቦ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፖለቲከኞች ከአውዳሚ የፖለቲካ ትግል ስልት በመውጣት ልዩነትን በዲሞክራሲያዊ መንገዶች መታገል ይገባል” የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ
Next articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከዞንና ወረዳ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።