
ከሚሴ: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የውይይት ኮንፈረንስ አካሄዷል።
በውይይት መድረኩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የብሔረሰብ አሥተዳደሩና የወረዳዎች መሪዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሩ አህመድ አሊ ፖለቲከኞች ከአውዳሚ የፖለቲካ ትግል ስልት በመውጣት ልዩነትን በሰላማዊ መንገድና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች መታገል ይገባል ብለዋል።
የወቅቱ ፈተና የኾነው ፅንፈኝነት ብሔርም ድምበርም የሌለው መኾኑን ገልፀው ለመታገል በመግባባት አቋም የሚያዝበት ኮንፈረንስ ነው ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኀላፊ ከድር አሊ የኮንፈረንሱ ዓላማ ምላሽ ያላገኙ የኅብረተሰብ ጥያቄዎችን በመለየት ችግሮቹን በመፍታት መልስ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የብሔረሰብ አሥተዳደሩን የልማት ሥራዎች ለማፋጠንና የሕዝብን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ወጥ አቋም የሚይዙበት ኮንፈረንስ እንደሚኾን እንጠብቃለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!