“ትግላችን የእውነትና የፍትሕ በመኾኑ የሕዝባችን ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኝ በትኩረት እንሠራለን ” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ

67

ሁመራ: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ)”ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን ” በሚል መሪ መልእክት በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የዞን ፣ የወረዳና የከተማ አሥተዳደር መሪዎች ኮንፈረስ እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወልቃይት ጠገዴ ሰተቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ትግላችን የእውነትና የፍትሕ በመኾኑ የሕዝባችን ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኙ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።
በሀገረ መንግሥት ምስረታ የአማራ ሕዝብ አያሌ መስዋዕትነትን መክፈሉን ያነሱት አቶ አሸተ በተሳሳተ ትርክት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በሀሳብ አንድነት እየፈታን እንሻገራለን ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብን ያለ መሪ ለማስቀረትና ለመበተን የሚሠሩ ጽንፈኛ ኀይሎችን ከመላው ሕዝባችን ጋር ልንታገላቸው ይገባል ያሉት አቶ አሸተ ለሀገር የከፈልነውን መስዋዕትነት ዛሬም በቁርጠኝነትና በአንድነት ልናስቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ እግዚአብሔር ደሴ የኮንፈረንሱ መሠረታዊ ዓላማ ለውጡን የማጠናከርና የማፅናት ጉዞን በጥልቀት መገምገም፣ የተመዘገቡ ለውጦችን ቆጥሮ ማስፋት እና ድክመቶችን ማረም የሚያስችል ነው ብለዋል።

ውስጣዊ አንድነትን በመፍጠር የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም ማስፈንና የሕግ የበላይነትን ማስከበር የሚያስችል የውይይት ኮንፈረንስ ነው ያሉት አቶ ገብረ እግዚአብሔር የልማት ሥራውን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ጠንካራ ፓርቲና መንግሥት መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።

የውይይት ኮንፈረንሱ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚዘልቅ ሲኾን በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል።
በውይይት ኮንፈረንሱም የአማራ ሕዝብን ከውድቀት ለመታደግ መስዋዕትነት ለከፈሉ ወገኖች ጧፍ ማብራትና የህሊና ጸሎት መታሰቢያ ተደርጓል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገር የሚገነባው በትምህርት ቤት ነው።” የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
Next article“ፖለቲከኞች ከአውዳሚ የፖለቲካ ትግል ስልት በመውጣት ልዩነትን በዲሞክራሲያዊ መንገዶች መታገል ይገባል” የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ