“ሀገር የሚገነባው በትምህርት ቤት ነው።” የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

91

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲዩት “የዩኒቨርሲቲዎች እና የኢንዱስትሪዎች ትስስር ለሀገር እድገት” በሚል መሪ መልዕክት 11ኛው ኮተን፣ ቴክስታይል እና አልባሳት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

በኮንፈረንሱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ሀገር የሚገነባው በትምህርት ቤት ነው ብለዋል። ዜጎችን ሳንገነባ ሀገር መገንባት አይቻልም ብለዋል።
አቶ መላኩ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ምሁራንን፣ መምህራንን እና ተመራማሪዎችን በማፍራት የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል። አሁንም እየተወጣ ነው ብለዋል። በተለይ የቴክኖሎጂ ኢንስቲዩቱ ለሀገር ግንባታ የነበረው ድርሻ ትልቅ ነበር ብለዋል።

ዓለም በቴክኖሎጅ የላቀ እና የረቀቀ ደረጃ ላይ ደርሳለች። በዚህ ጊዜ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እና ባዮ ቴክኖሎጂው መካከል ከፍተኛ ልዩነት እየተፈጠረ ነው። ይህን ልዩነት ለማጥበብ ትምህርት ቤቶች ላይ በጥልቀት ሊሠራ ይገባል ብለዋል። የታሠበችውን ሀገር ለመገንባት ዩኒቨርሲቲዎችን እና ትምህርት ቤቶችን መደገፍ ተገቢ ነው ብለዋል።

ታሪክ መነሻ እንጅ መድረሻ አይደለም። ሥለዚህ መድረሻችንን የምንሠራው በትምህርት ቤቶች ነው ብለዋል።

የቴክኖሎጅ ኢንስቲዩቱ ለሀገር እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ፈተናዎችን በብልሃት ማለፍም ተገቢ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ ሰፊ የጥሬ እቃ መገኛ በመኾናቸው ይሕን ጥሬ እቃ ወደ ምርት በመቀየር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መኾን እንደሚገባም አንስተዋል።
አቶ መላኩ ባለፉት ኮንፈረንሶች የነበሩ ችግሮችን በማንሳት መወያየት 11ኛውን ኮንፈረንስ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና አምባሳደር የሺ መብራት (ዶ.ር)ን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና የኢንዱስትሪ ባለቤቶች በዘርፉ የተሠማሩ አካላት እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካ ኅብረት ምስረታውን ሲያከብር ለአፍሪካውያን ሰላም፣ ደህንነት እና እድገትን ለማምጣት በመትጋት መኾን ይገባዋል ሲሉ የኅብረቱ ሊቀመንበር ገለጹ።
Next article“ትግላችን የእውነትና የፍትሕ በመኾኑ የሕዝባችን ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኝ በትኩረት እንሠራለን ” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ