
ደሴ ፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ” ፈተናወችን ወደ ዕድል በመቀየር ፤ ሕዝባችንን እናሻግር ” በሚል መሪ ሀሳብ በወቅታዊ ጉዳዮች እና የቀጣይ መፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ በደሴ ከተማ መካሄድ ጀምራል።
የፕሮግራሙ መክፈቻ የተጀመረው በቅርቡ ህይወታቸውን ላጡት ለአቶ ግርማ የሽጥላ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግና የጎህ ቃል ኪዳንን ለማስታወስ የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት በማካሄድ ነው።
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ አሥተዳድር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ከዋልታ ረገጥ እሳቤዎች በመውጣት ዘረኝነት በፅኑ ልንታገል ይገባል ብለዋል። መሪን በመግደል የሚመጣ ለውጥ የለም፤ ተበታትነን ሳይሆን አንድ ሁነን ለለውጥ መትጋት አለብን ብለዋል።
የኮንፈረንሱን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድርያስ አብዱ ተለዋዋጭ የሆነውን የፓለቲካ ሁኔታ መመከት የሚቻለው አንድ በመሆንና ለጋራ ዓላማ በጋራ በመቆም ነው ብለዋል።
በተለዋዋጭ አጀንዳዎች መወጠር፣ ቁርጠኛ አለመሆን፣ ፅንፈኛ አስተሳሰቦች እንዲሁም የአንድነት መላላት እና መሰል ጉዳዩች ለክልሉ ፈተናዎች መሆናቸውን አንስተዋል። በቀጣይ አስተሳሰብ ላይ በመሥራት የማይቀለበስ ለውጥ በማምጣት ልናስወግደው ይገባል ብለዋል።
አቶ እንድርያስ አክለውም ትልቁ ችግራችን ፅንፈኝነት ነው፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ አብሮነትን የሚያሳድጉ ልማዶችን ማዳበር ይገባል ሲሉ በአፅንኦት ገልጸዋል። ውስጣዊ ተጽእኖዎችን በመቀልበስ ውጫዊ ችግሮችን በመመከት ጠንክረን መቆም አለብንም ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሆኑት ከሕገ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች፣ የወሰን ጉዳይ፣ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ሕዝቦች መብት እና መሰል ጥያቄዎች በጋራ የምክክር ኮሚሽኑ እንደሚፈቱ ይታመናል ብለዋል።
እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የመንግሥት ሚና እንዳለ ሁኖ ሕዝባችንም ከጎናችን መቆም ይኖርበታል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!