
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ “ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችን እናሻግራለን” በሚል መሪ ሐሳብ ድርጀታዊ ኮንፈረንስ ጀምሯል።
ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በተገኙ ድሎች እና ባጋጠሙ ፈተናዎች ዙሪያ ውይይት እና የቀጣይ ጊዜ አቋም ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በግልጽ የሚታዩ እና ተጨባጭ ለውጦች ታይተዋል ያሉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የተገኙትን ተጨባጭ ድሎች በሚፈለገው ፍጥነት አለማስቀጠል እና ለሚፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮች ፈጣን ምላሽ አለመስጠታችን ለአሁናዊው ችግሮች ምክንያት ኾነዋል ብለዋል።
በሀገሪቱም ኾነ በክልሉ እየተፈጠሩ ላሉ አሁናዊ ችግሮች ቀዳሚውን ኅላፊነት መውሰድ ያለብን እኛ የፖለቲካ መሪዎቹ ነን ያሉት ዶክተር ድረስ “ከውጫዊ ፈተናዎቻችን ይልቅ ወስጣዊ ልዩነቶቻችን ዋጋ እያስከፈሉን ነው” ብለዋል። የሐሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ ለማያባራ ግጭት ምክንያት በሚኾን መንገድ የኃይል አማራጮችን መጠቀም ለመጨረሻ ጊዜ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የፖለቲካ አመራሩ በዚህ ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ በገጠሙን ችግሮች ዙሪያ በግልጽ መወያየት ይጠበቅበታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በኮንፈረንሱ መጨረሻ ላይም አቋም መያዝን ይጠይቃል ነው ያሉት።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እስካሁን የነበሩት የለውጥ መንገዶች አመራሩ ግልጽ ባልሆኑ እና በተስረከረኩ እሳቤዎች ውጣ ውረድ የበዙበት እንደነበር አንስተው ከዚህ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ማግስት ከሕዝብ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ችግሮችን ማጥራት ይጀመራል ብለዋል። በመሆኑም አመራሩ የአቋም እና የአፈጻጸም ዝግጁነት ማድረግ እንደሚኖርበት አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!