የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች በዉይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች።

61

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ 16 ቀናት ሲያካሒድ የነበረውን ምልዕተ ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ሲኾኑ ሲኖዶሱ የተለያዩ ዉሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ሲኖዶሱ በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ እና አሥተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሰይሞ በሥራ የሚገኘው ልኡክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች ላይ በተፈጠሩ ችግሮች ካህናት ለእስር እና ለእንግልት እየተዳረጉ በመኾኑ ችግሮች እንዲቀረፉና ወደ መደበኛው የአሠራር መዋቅር እንዲመለሱ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን በመሠየም ከፌዴራልና ከኦሮሚያ መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ዉሳኔ አሳልፏል ተብሏል።

በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ የሚያስችል 20 ሚሊዮን ብር እንዲሰጥም ወስኗል።

በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶችም በዉይይት እንዲፈቱ ቤተክርስቲያኗ ጥሪ አስተላልፋለች።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ214 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ማምረት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው – ግብርና ሚኒስቴር
Next articleየአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ከመስከረም ጀምሮ ሊሰጥ ነው።