በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ214 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ማምረት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው – ግብርና ሚኒስቴር

78

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ214 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ማምረት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በሁሉም ሥነ-ምህዳር በቀላሉ ተመርቶ ከፍተኛ ጥቅም በሚያስገኘው የውኃ ግብርና ዘርፍ ባለሃብቶች እንዲሰማሩ ተጠይቋል።

የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት(ፋኦ) እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2020 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ በውኃ ግብርና ወደ 123 ሚሊዮን ቶን የዓሣ ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፤ በገንዘብ ሲሰላ 282 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያም ምግብን በጓሮ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እስከ 2018 ዓ.ም የሚቆይ “የሌማት ትሩፋት” መርሐ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ከታቀፉት የግብርና ሥራዎች መካከል የውኃግብርና በተለይም የዓሣ ምርት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

በግብርና ሚኒስቴር የዓሣ ሀብት ልማት ዴስክ መሪ ዶክተር ፋሲል ዳዊት፤ አኳካልቸር በተለምዶ ከዓሣ ጋር ይያያዝ እንጂ አልጌ፣ የባሕር ውስጥ ተክሎች እንዲሁም ‘ክሩስቴሽያን’ እና ‘ሞሉስክ’ ጨምሮ ሌሎች የጀርባ አጥንት የሌላቸው ጥቃቅን እንስሳትን የሚያካትት መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች በቅርብ የተገነቡ ግድቦችን ሳይጨምር በዓመት 94 ሺህ ቶን ዓሣ ማምረት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
የውኃ ግብርና ውስን ሀብትና ገንዘብ በማንኛውም የውኃ ሥነ-ምህዳር ማምረት የሚቻል ቢሆንም ከዓሣ ምርት ውጭ ትኩረት ተሰጥቶ አልተሰራበትም ብለዋል።

በተለይም አልጌ በቀላሉ የሚመረት ለምግብነት የሚውል ከፍተኛ ይዘት ያለውና ለመድኃኒትነት የሚያገለግል ቢሆንም እምብዛም አልተሰራበትም ነው ያሉት ዶክተር ፋሲል።
በሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር የውኃ ግብርናን በተለይ ዓሣና አልጌን በስፋት በማምረት የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገቢ ለማመንጨት በመንግሥት በኩል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ለሁሉም ሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የዓሣ ዝርያዎች እንዳሉ ገልጸው፤ እንደ ሀገር በ1 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር ቦታ ላይ ዓሣ ማምረት ይቻላል ብለዋል፡፡

አምራቾችና የግል ባለሃብቶችን ጭምር በማሳተፍ እስከ 2018 ባሉ ሶስት ዓመታት በየዓመቱ 214 ሺህ ቶን ዓሣ ለማምረት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
የውኃ ግብርና እንደ ዶሮ፣አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶችን ጎን ለጎን ማምረት የሚያስችል ቀላል እንዲሁም ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓሣ ከተመረተ በኋላ ለምግብነት የሚውለው ከተረፈ ምርቱ ሲለይ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፤ ለአብነት የዶሮ 48 በመቶ፣ አሳማ፣ በግና ፍየል ደግሞ ከ30 በመቶ አይበልጥም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም በአርሶ አደሩ ዘንድ ገቢራዊ የሚደረገው የዓሣ አመራረት ዘዴ ምንም እንክብካቤ ሳያደርጉ ውኃና ዓሣን በማገናኘት ብቻ የማምረት ሂደት መሆኑን ነው ዶክተር ፋሲል ያስረዱት።

በሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር የአርሶ አደሩንም ሆነ በዘርፉ የሚሳተፉ ባለሃብቶችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ በመንከባከብ ሂደት የማምረት ስልት እንዲከተሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም ባለሃብቶች ለውኃ ግብርና ያለውን ምቹ ሥነ-ምህዳር እና የዓሣ ዝርያ በመጠቀም ገቢያቸውን ማሳደግና ኢኮኖሚውን መደገፍ የሚችሉበትን ዕድል እንዲጠቀሙም ባለሙያው ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በ2015 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ 541 ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሔደ ነው” የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ
Next articleየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች በዉይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች።