ተጠፋፍተው የነበሩ ወላጅና ልጅ ከወራት በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ተገናኙ፡፡

60

ደሴ፡ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሕፃን ረድኤት ዘሩ የሦስት ዓመት እድሜ ታዳጊ ስትኾን በደሴ ከተማ ሆጤ ክፍለ ከተማ 07 ቀበሌ ከጓደኞቿ ጋር እየተጫወተች ባለበት ጊዜ ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር ባልታወቁ ሰዎች የተወሰደችው።

በደሴ ከተማ አስተዳደር 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሴቶችና ሕፃናት ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ማንጠግቦሽ ደሴ ከሥራ ሲመለሱ ነበር የልጃቸውን መጥፋት የሰሙት።

በሁኔታው የተደናገጡት የረድኤት ቤተሰቦች በጊዜው ፍለጋ ቢያደርጉም ሊያገኟት አልቻሉም ነበር። በቀጣይ ቀናቶች በራዲዮና በተለያዩ ማስታወቂያዎች የማፈላለጉን ሥራ ቢሠሩም ሕፃን ረድኤትን አየሁ የሚል ጠፋ። የአካባቢው የፀጥታ ኀይልና የአካባቢው ነዋሪ ፍለጋውን ቢያጠናክርም የሕፃኗ ጉዳይ የውኃ ሽታ ሁኖ ቀረ። ቀናት ቀናትን እየወለዱ ወራት በወራት እየተተኩ ለአስራ አንድ ወር ያክል ሳትገኝ ቀረች።

አባት ዘሩ ሰይድ እና እናት ምክትል ኮማንደር ማንጠግቦሽ ደሴ የልጃቸው ጉዳይ ተስፋ የሚሰጥ ባለመኾኑ ቅስማቸው ተሰብሮ በቤታቸው ተቀመጡ። ጉዳዩ በመጨረሻም በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ከተያዘ በኋላ እንደ አማራጭ በማኅበራዊ ሚዲያ ዳግም ልጅቱን የማፈላለግ ሥራ መሥራት ተጀመረ። በዚህም በደሴ ከተማ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንና በደሴ ብልጽግና ፓርቲ ይፋዊ የፌስቡክ ገጾች የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ከሕፃኗ ፎቶ ጋር ተያይዞ ተለጠፈ።

ጉዳዩን የተመለከቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ለበርካታ ሰዎች ማጋራታቸውን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ልጅቱን አየሁ የሚል ጥቆማ ተሰማ። በእናት ማንጠግቦሽ ደሴ የተደወለ ስልክ ልጅቱ አዲስ አበባ እንዳለችና በቦሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ለወራት ያክል ለልመና አንዲት ሴት እየተጠቀመችባት እንደኾነ ተነገራት። ይህ ጥቆማ ለወራት የልጃቸው መጥፋት ሀዘን ለገባቸው ቤተሰቦች ተስፋን የሰጠ ነበር።

የልጅቱም ቤተሰቦች አዲሰ አበባ ለሚያውቋቸው ሰዎች ስለጉዳዩ በማስረዳት ሕፃን ረድኤት ዘሩንና እየለመነችባት ነው የተባለችው ግለሰብ እንድትያዝ በስልክ ተናገሩ። ጉዳዩን ለአካባቢው ፖሊስ ካሳወቁ በኃላ ግለሰቧ በቁጥጥር ስር ዋለች።
አዲስ አበባ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የጠፋችው ትክክለኝ ልጃቸው መኾኗን ለማረጋገጥ የሕፃን ረድኤት ፎቶ ለወላጆቻቸው ይልካሉ። ስለ ሁኔታው ለአሚኮ የተናገሩት እናት ማንጠግቦሽ “የልጄን ፎቶ ስመለከት ጥርጣሬ ገብቶኝ ነበር” ብለዋል።
“ልጄ ለወራት ያክል በደረሰባት እንግልትና ስቃይ መቀየሯ ታውቆኛል” ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን በአካል ሂደው ማየትና ማረጋገጥ የፈለጉት ወላጆቹ ወደ አዲስ አበባ ሄዱ። “ገና ከርቀት እንዳየኋት ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ እንባዬም መፍሰስ ጀመረ” የሚለው ወላጅ አባት ዘሩ ሰይድ ፈጣሪ ዳግም እንደ ፈጠረኝ ነው የማምነው ሲል ነበር ስሜቱን የገለጸው።

ለወራት ከልጃቸው የተለዩት እኚህ ወላጆች ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም ደሴ ከተማ ሲገቡ በደሴ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸውና ስለ ጉዳዩ በሰሙ በከተማይቱ ነዋሪዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በቤታቸው ተገኝተው እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ማኅበራዊ ሚድያን በአግባቡ ከተጠቀምን እንዲህ ልጅን ከቤተሰብ ማገናኘት ይቻላል ብለዋል።

ወንጀለኞችን ለመከላከል ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ያሉት ከንቲባው ለወራት በልጃቸው መጥፋት ቅስማቸው ለተሰበረው ቤተሰብ ከተማ አሥተዳደሩ የቤት ስጦታ እንዳዘጋጀላቸውና በፈለጉት ጊዜ መረከብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከተማ አሥተዳደሩ ቤተሰቡ በሚያስፈልገው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መኾኑን ነው አቶ ሳሙኤል የተናገሩት።

አሚኮ ከሕፃን ረድኤት ዘሩ ቤተሰቦች ባገኘው መረጃ መሰረት ጥቆማውን የተናገረችው ምታምር በለጠ እንደምትባል እና በአዲስ አበባ በሊስትሮ ሥራ ላይ የተሰማራች ስለመኾኗ ለመረዳት ተችሏል። ጥቆማውን ላደረሰችው የደሴ ከተማ አሥተዳደር የ50 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያደርግ ገልጿል። ሕፃን ረድኤት ዘሩን በመስረቅና ለልመና ስትጠቀምባት የነበረችው ወይንሽት መኮንን የተባለችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተደረገባት ይገኛል።

የሕፃን ረድኤት ወላጆች በጭንቅ ጊዜ አብረዋቸው ለተጨነቁ፣ በፍለጋ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከጎናቸው ለነበሩ የ07 ቀበሌ ነዋሪዎችና ጎረቤቶቻቸው ፈጣሪ ውለታቸውን ይክፈልልን ብለዋል። ለልጃቸው መገኘት ምክንያት ለኾኑላቸው የደሴ ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽንና ለብልጽግና ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ከፍተኛ ምሥጋናም አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል” የዓለም ባንክ
Next article“በ2015 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ 541 ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሔደ ነው” የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ