
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማነት እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እና ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እንድታስመዘግብ የፋይናንስ እና የሙያ ድጋፍ እያቀረበ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ እንዲሁም የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ገቢራዊ እንዲሆን የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።
ባንኩ የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በባንኩ የፋይናንስ ተወዳዳሪነት እና ኢኖቬሽን ዓለም አቀፍ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አልዋሊድ ፋሬድ አልታባኒ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚስተዋለው ለውጥ አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማስፋት እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላታል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን እና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ የሚያከናውናቸው ተግባራት ባንኩ በአድናቆት እንደሚመለከተው ጠቁመዋል።
የዓለም ባንክም ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና አገሪቱ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እንድትገነባ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ምርት አስፈላጊ የሆኑ የግብዓት እጥረትን መፍታት የሚያስችል ጥሬ ዕቃዎች በስፋት እንደሚገኙ ገልጸው፤ እነዚህ ጥሬ ዕቃዎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ግብዓት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ ከሌሎች ፋብሪካዎች ጋር ትስስር የመፍጠር ሥራ በማከናወን ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራ በማሳደግ፣ የውጭ ንግድ አፈጻጸምን በማስተካከል እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የአገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም መግለጫቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!