
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቢቸና ከተማ አሥተዳደር በዓለም ባንክ እና በመንግሥት በጀት የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ የውኃ ማፋሰሻ ቦይ፣ የወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ሸድ፣ ፓርኪንግ፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍትና የጠጠር መንገድ ፕሮጀክቶችን መተግበሩን ገልጿል፡፡
በከተማዋ የ02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተፈራ ማዕምር እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከክረምት ጭቃ እና በጎርፍ ከመበላት እንዳዳኗቸውም ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ሥራውን በመደገፍ በኩልም ድርሻ ነበረው፣ ለወጣቶች ውኃ በነጻ ከመፍቀድ የቁሳቁስ ማከማቻ ቤቶችን እስከ መሥጠት እገዛ ሰለማድረጋቸው ነግረውናል፡፡
ማኅበረሰቡ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ አካባቢውን ከ3ኛ ወገን ነጻ በማድረግ ከወጪ ማዳኑንም ነው ያነሱልን፡፡ ሱቅና አጥር በራሳቸው ጊዜ ያነሱ ነዋሪዎችንም አመሥግነዋል፡፡
ሌላኛዋ የቢቸና ከተማ አሥተዳደር የምክር ቤት አባል ወይዘሮ መንበረ አለማየሁ፤ ፕሮጀክቶቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ የዘመናት ችግሮችን የፈቱ ናቸው ብለዋል፡፡
ወይዘሮ መንበረ እንዳሉት የተሠሩ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያፋጥኑ ናቸው፡፡ በተለይ የእጅጉ ዘለቀ ፋውንዴሽን የወጣቶች መዝናኛ እና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ግንባታዎች የማኅበረሰቡን ችግር የፈቱ ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡
የመንገዶች መገንባት ባለሃብቶች ወደ ወረዳዋ እንዲመጡ አስችሏልም ብለዋል፡፡
የቢቸና ከተማ አሥተዳደር የከተሞች ተቋማዊ እና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጥበቡ አበበ፤ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ነግረውናል፡፡
ፕሮጀክቶቹ 39 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የወሰዱ ሲኾን 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ከዓለም ባንክ የተገኘ ድጋፍ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
የቢቸና ከተማ አሥተዳደር 17 አዳዲስ እና 8 ነባር ፕሮጀክቶችን በድምሩ 25 ፕሮጀክቶችን ለመሥራት አቅዶ 15 አዳዲስ እና 8 ጥገና በድምሩ 23 በማድረግ አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ክፍት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ያልተጠናቀቁት እና የውል ጊዜያቸው ገና የኾኑት ፕሮጀክቶች እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ሠርቶ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ጥበቡ ሥራው በወቅቱ እና በጥራት እንዲጠናቀቅ በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ማኅበረሰብ ያደረገው ድጋፍ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ለ961 ወጣቶች ቋሚ እና ጊዜአዊ የሥራ እድል መፍጠራቸውን ነግረውናል፡፡
ሥራው በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ከ69 ሺህ በላይ ለኾነው የከተማ አሥተዳደሩ ነዋሪ ተጠቃሚ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡
አቶ ጥበቡ ተግባብቶ፣ ተስማምቶ እና ተወያይቶ መሥራት ሥራው በወቅቱ እንዲጠናቀቅ አስችሎናልም ብለዋል፡፡ ቀጣይ በሚደረጉ የልማት ሥራዎች ማኅበረሰቡ የተጠናከረ ድጋፉን እንዲቀጥልም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!