ከተማ ሲታወስ – አህጉራዊ ልዩነትን እና መራራቅን ያጠበበ መሐንዲስ!

115

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የትውልድ ቀየው በሃረር ጠቅላይ ግዛት ውስጥ እንደነበር ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያዊው ፓን-አፍሪካኒስት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ገና ወደ ዙፋን ሳይመጡ 1922 ዓ.ም ላይ ነበር የተወለዱት፡፡ አህጉራዊ ኅብረት እና ነጻነት አጥብቆ በሚፈለግበት በዚያ ወቅት ወደዚያች ምድር የመጣው ብላቴና የኋላ ኋላ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካ የምትፈልገው የልጅ ሽማግሌ ለመኾን በቅቷል፤ ወጣቱ እና ኢትዮጵያዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ከተማ ይፍሩ፡፡

በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት ልጅ የነበሩት ክቡር ከተማ ይፍሩ የልጅነት ዘመናቸው በስደት ያለፈ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሱማሌ-ላንድ በኋላ ደግሞ በኬንያ የመከራውን ዘመን በግዞት ለማሳለፍ ተገድደዋል፡፡ ከነጻነት ማግስት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሀገረ አሜሪካ አቅንተው ቦስተን ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ የሶስተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ ዕድሎች ቢመቻችላቸውም ወደሀገሬ መመለስ እፈልጋለሁ ሀገሬ ትፈልገኛለች ብለው ተመለሱ።

ከትምህርት ማግስት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካ እና የኢስያ ክፍል ኅላፊ በመኾን 1945 ዓ.ም ብርቱውን እና ውጤታማውን የሥራ ዘመናቸውን ጀመሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምረውም እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ፀሐፊነት ድረስ በተለያዩ ዘርፎች እየተመደቡ ውጤታማ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ታላቁን የሀገር እና የሕዝብ የኅላፊነት ቀንበር በልጅነታቸው የመሸክም አቅም ያዳበሩት ክቡር ሚንስትር ከተማ ይፍሩ በንጉሠ ነገሥቱ ሳይቀር የተደነቁ እና እምነት የሚጣልባቸው “የልጅ አዋቂ” ለመባል በቁ፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ሙሉ እምነት እና ይሁንታን ያተረፉት ወጣቱ የፖለቲካ ምሁር ክቡር ከተማ ይፍሩ 1953 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኾነው ተሾሙ፡፡ በዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ላይ ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው የመሰብሰብ ዕድል ያገኙት ክቡር ከተማ ይፍሩ ያገኗቸውን ዕድሎች በመጠቀም ሀገራቸውን ከቀሪው ዓለም ዘንድ ከማስተዋወቅ ባለፈ የዓለም ፖለቲካ ጎራ አሰላለፍን በአግባቡ ለማጤን የሚችሉበትን ዕድል አገኙ፡፡ ከልምድ እና ነባራዊ ሁኔታ የሚገኝ ዕውቀት በሚያስፈልግበት በዚያ ዘመን በተለያዩ የዓለም ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች መሳተፍ የቻሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፍሪካ የሚያሻት እና የሚያስፈልጋት የትብብር መንፈስ እንደኾነ በሚገባ አጤኑ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር ሚንስትር ከተማ ይፍሩ ወደ ሥልጣን እና ኅላፊነት የመጡበት ወቅት በአፍሪካ አህጉር አዲስ የፖለቲካ ድባብ እና መንፈስ የሚስተዋልበት ወቅት ነበር፡፡ እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ስሌት የ1950ዎቹ መጨረሻ እና 1960ዎቹ መግቢያ በአፍሪካ አሕጉር የለውጥ ነፋስ የነፈሰበት ዘመን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለይም 1960ዎቹ በርካቶቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ የወጡበት በመኾኑ “የአፍሪካ ዘመን” እየተባለም ይጠራል፡፡ የነጻነት ችቦ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር በፍጥነት በሚሸጋገርበት በዚህ ወቅት የአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ተምሳሌት የኾነችን ሀገር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መምራት ተራማጅነትን አብዝቶ የሚጠይቅ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ ቢወጡም ከድህረ ነጻነት ጀምሮ ያለው አፍሪካዊ ኅብረትን የመመስረቱ ጉዞ በልዩነቶች የታጠረ ነበር፡፡ መጻዒዋ አፍሪካ ነጻ አህጉር መኾን ይኖርባታል በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ልዩነት ባይኖርም ወደ አህጉራዊ ኅብረት ለመምጣት መንገዶቹ በዋናነት ለሁለት ተከፈሉ፡፡ የካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ ቡድኖች የአፍሪካ መጻዒ አህጉራዊ ነጻነት በሌሎች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው የሚሉ እና አፍሪካ ነጻ አህጉር ለመኾን የማንንም በጎ ፈቃድ እና ትብብር አትሻም የሚሉ ኅይሎች ጎራ ለይተው ተሰለፉ፡፡ የአፍሪካ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውሕደት ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ በመኾኑ ወዲያውኑ መጀመር አለበት የሚሉና ውሕደቱ አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜ ያስፈልገዋል በሚሉና በሌሎች እሳቤዎች ዙሪያ ልዩነቱ ሰፋ።

ለዘመናት ነጻነቷን ሳታስደፍር የቆየችው ኢትዮጵያ ከሁለቱም ጎራ የተሳትፎ ጥሪ ቢቀርብላትም የመጻዒውን ኅብረት ያሰቡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ 22 የአፍሪካ ሀገራትን ያቀፈውን የሞኖሮቪያ ቡድን ጥሪ እንደተቀበሉ እና የሌጎስን ጉባዔ ቻርተር መፈራረማቸውን ለንጉሠ ነገሥቱ ነገሯቸው፡፡ “የተሻለ የምትለውን አንተ ምረጥ” የሚል ይሁንታን ከንጉሠ ነገሥቱ ያገኙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሁለቱን ጎራ በማሰባሰብ አህጉራዊ ኅብረት መፍጠር እንዳለባቸው ስላመኑ ለተፈጻሚነቱ በትጋት ይሠሩ ነበር፡፡

“ንጉሠ ነገሥቱ እና ኢትዮጵያ በጀኔቭ የደረሰባቸውን ብቸኝነት ዳግም በአፍሪካ ሀገራት ደርሶ ማየት የለብንም” የሚል ጽኑ አቋም የሚያራምዱት ክቡር ከተማ ይፍሩ የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድኖችን የጎራ ልዩነት በመናድ ወደ አንድ ለማምጣት ከሀገር ሀገር መንከራተቱን ተያያዙት፡፡ ከንጉሠ ነገሥታቸው ጋር ተነጋግረው አፍሪካ አንድ ጠንካራ ኅብረት መመስረት ያስፈልጋታል በሚለው ሃሳብ ድምዳሜ ላይ የደረሱት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን ለማግባባት የንጉሠ ነገሥቱን የጥሪ ደብዳቤ ይዘው ለሁለት ሳምንታት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ተመላለሱ፡፡

የጋናውን ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ፣ የግብጹን መሪ ገማል አብድል ናስር፣ የናይጀሪያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ታፋዋ ባሌዋ፣ የሞሮኮን ንጉሥ ሐሰን፣ የታንዛኒያውን ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬን እና የሌሎችን ሀገራት መሪዎች በማግባባት ኅብረቱን ለመመስረት ቀን አስቆረጡ፡፡ 32 ከቅኝ ግዛት ነጻ የኾኑ ሀገራት የኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብለው በምስረታ ጉባዔው ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ እንደሚገቡ አስታወቁ፡፡

የዓለም ሕዝብ ዐይን ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ተመለከተ፤ የዓለም ሕዝብ ለአዲስ አበባ ጆሮውን አዋሰ፡፡ ከ250 ሺህ በላይ አፍሪከዊያን እጅግ በጋለ ስሜት የሚጠብቁት የአህጉሪቷ ድርጅት ምስረታ ግንቦት14/1955 በአፍሪካ አዳራሽ ተጀመረ፡፡ ከሁሉም የዓለም ክፍል የመጡ እና ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሚኾኑ ጋዜጠኞች በቅርበት እና በትኩረት እየተከታተሉ ጉዳዩን ለዓለም ሕዝብ ያደርሳሉ፡፡

አህጉራዊ ልዩነትን እና መራራቅን ያጠበቡት መሐንዲስ ክቡር ሚንስትር ከተማ ይፍሩ ጥረታቸው ሰምሮ 32ቱ ሀገራት ግንቦት 17/1955 ዓ.ም የያኔውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የወቅቱን የአፍሪካ ኅብረት መመስረቻ ቻርተር ተፈራርመው አጸደቁ፡፡ ክቡር ከተማ ይፍሩ ከዚህ ድርጅት ምስረታ ጀርባ የነበሩ የጀርባ አጥንት ተደርገው ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

ምንጭ፡- ቀኃሰ እና የአፍሪካ ኅብረት በኤርሚያስ ጉልላት እና የአፍሪካ ታሪክ ዳሰሳ

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleካለፉት ዓመታት የተሻለ ጎብኝዎች ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ መምጣታቸውን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
Next articleበተሠሩ ፕሮጀክቶች ከዘጠኝ መቶ በላይ ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉን የቢቸና ከተማ አሥተዳደር ገለጸ፡፡