ካለፉት ዓመታት የተሻለ ጎብኝዎች ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ መምጣታቸውን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

64

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ብሔራዊ ፓርኩ የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር መሻሻል እያሳየ መኾኑን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ብርቅ የኾኑ እንስሳት የሚገኙበት፣ አምላክ ያሳመሯቸው ውብ ተራራዎች የመሉበት፣ ምንጮች ክረምት ከበጋ ባዘቶ እየመሠሉ የሚፈስሱበት፣ ደጋግ፣ ኩሩና ጀግኖች ያሉበት፣ የተፈጥሮ ውበት በእጅጉ የመላበት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የዓለምን ቀልብ ይስባል፡፡

ማንም ሳይናገርለት፣ ማንም ሳይጽፍለት፣ ማንም ስለ ውበቱ ሳይመሰክርለት በውበቱ ሕዝብን ይጠራል፤ በግርማው እያማለለ ያሰባስባል፡፡ ለሰማይ የቀረቡ የሚመስሉትን የራስ ደጀን ተራራዎችን፣ በገደላማው ሥፍራ የሚመላለሱትን ዋልያዎች፣ ቀይ ቀበሮዎችንና ጭላዳ ዝንጀሮዎችን፣ እጅግ የረቀቁ ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሥፍራዎችን ማዬት የሚሹ ጎብኝዎች ረጅም ኪሎ ሜትሮችን እያቆራረጡ ወደ ውቡ ሥፍራ ይገሰግሳሉ፡፡

በዚያም ሥፍራ በደረሱ ጊዜ መልካሙን ነገር እያዩ ይደሰታሉ፡፡ በዚያ ስፍራ ያዩትን ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ ሁሉ ያደንቃሉ፡፡ ሀገር ሰላም በኾነች ጊዜ በዚህ ውብ ሥፍራ የሚመላለሱ ጎብኝዎች ብዙ ናቸው፡፡ አንደኛው ጎብኝቶ ሲመለስ ሌላኛው እየተተካ ዓመቱን ሙሉ ጎብኝዎች የማይጠፉበት ሥፍራ ነው፡፡ ዳሩ አስቀድሞ ዓለምን ያሸበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ቀጥሎም ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ጦርነት ያን ተናፋቂ እና ያለ ጎብኝ የማያድረውን ሥፍራ ሰው አልባ አድርጎት ቆይቷል፡፡

በርካታ ጎብኝዎችም ድንቅ የተፈጥሮ ውበት የተቸረውን ሥፍራ ለማየት እየጓጉ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ በየቀኑ እንግዳ ማስተናገድ የማይሰለቻቸው የአካባቢው ደጋግ ሰዎችም እንግዳ ሲናፍቁ ኖረዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ስጋት መቀነስ እና የጦርነቱ ማቆምን ተከትሎ ጎብኝዎች ወደዚያ ተወዳጅ ሥፍራ እየመጡ ነው፡፡

የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዛናው ከፍያለው በርካታ ጎብኝዎችን በመሳብ የሚታወቀው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አስቀድሞ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳት እንደደረሰበት ነው የተናገሩት፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወቅት ጎብኝዎች ሙሉ ለሙሉ አቁመው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ማግሥት በተፈጠረው ጦርነት የቱሪዝም ፍሰቱ ሌላ ፈተና ገጥሞት እንደቆዬም ገልጸዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ በ2011 ዓ.ም 32 ሺህ የውጭ ሀገር ዜጎች ጎብኝተውት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት የቱሪዝም ፍሰቱ ቀንሶ እንደቆዬም ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ የጸጥታው ሁኔታ በመሻሻሉ የቱሪስት ፍሰቱም እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡ ያም ኾኖ ግን ከበፊቱ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል የቱሪስት እንቅስቃሴ ነው ያለው፡፡

ባለፉት ወራት ከባለፉት ዓመታት የተሻለ የቱሪስት ፍሰት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ ቱሪዝሙ እንደገና እንዲያገግም እና ወደ ተወዳጁ ሥፍራ ጎብኝዎች እንዲመጡ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በአካባቢው ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ስለሌለ ጎብኝዎች እየመጡ እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንግዶች ወደ ሥፍራው ሲመጡ ከወትሮው የተሻለ አመቺ ሥፍራዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። የቆይታቸው ጊዜ እንዲጨምርም ከዚያም አልፎ ለእግዶቹ ምቹ እንዲኾኑ በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡

አካባቢው በጦርነት በመቆየቱ ምክንያት በፓርኩ የሕግ መላላቶች ነበሩ ብለዋል ኀላፊው። በፓርኩ ዙሪያ ሕግ እንዲከበርና ፓርኩ እንዲጠበቅ ከፌዴራል ጀምሮ በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል፡፡ በፓርኩ ዙሪያ ካሉ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ፓርኩን የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲጠብቀውና እንዲንከባከበው እያደረጉ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል፡፡

በተለይም የክረምት ወራት መድረሱን ተከትሎ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ልዩ ውበትን እና ግርማን ይላበሳል፡፡ ከወትሮው በልዩ ግርማ ጎብኝዎችን የሚያስደስተው ድንቁ ምድር በክረምት አረንጓዴ ካባ ሲለብስ ከውበት ላይ ውበት ይደርባል፡፡ ለጎብኝዎችም ልዩ ደስታን ይፈጥራል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአማራ ክልል የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
Next articleከተማ ሲታወስ – አህጉራዊ ልዩነትን እና መራራቅን ያጠበበ መሐንዲስ!