
ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ያልተለየው፣ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገበት የሕዝብ ፕሮጀክት ነው፡፡
ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የአማራ ሕዝብ ተሳትፎም ከፍተኛ እንደነበር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡
ሕዝባዊ ድጋፉ በአማራ ክልል ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ መቀጠሉን የአማራ ክልል የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኃይለ ሚካኤል ካሳሁን ገልጸዋል፡፡
ኀላፊው እንዳሉት ባለፉት 12 ዓመታት የአማራ ክልል ሕዝብ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ አበርክቷል፤ በዚሕ ደግሞ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተሳትፏል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና ጦርነትም የማኅበረሰቡ ድጋፍ አለመቆሙን ነው ያነሱት፡፡ በ2015 ዓ.ም ለመሰብሰብ ከታቀደው 20 ሚሊዮን ብር 77 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ የሴቶችና ወጣቶችን ሊግ ያሳተፈ የቦንድ ግዥ ንቅናቄ እየተካሄደ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ በሀገር ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ያነሱት ኀላፊው አሁንም የሕዳሴው ግድብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ እውን እስኪኾን ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!