
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበራዊ ጥበቃ ለሰብዓዊ መብት እና ደህንነት መሰረት የሚጥል እና የመንግሥትን ማኅበራዊ ውል ከሕዝቡ ጋር የሚያስተሳስር ቁልፍ ተግባር መኾኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ “ማኅበራዊ ጥበቃ ለሃገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል እየተደረገ ባለው ማኅበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዓለማችን ባለፉት ዓመታት ኮቪድን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች የገጠሟት ሲሆን ይህም የማኅበረሰብን መስተጋብር መፍረስ ገጥሟት ቆይታለች ብለዋል።
አክለውም፣ ሀገራችን በሰው ሥርራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ሰፊ ጉዳት እንደደረሰባት አንስተዋል። እነዚህ ችግሮች የሕዝባችንን ኑሮ አደጋ ላይ የጣሉ በመኾናቸው ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ እንደሚያሻ ገልጸዋል።
መንግሥትም የሁሉንም ዜጎች ደህንነት ለመጠበቅ እና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስቀጠል እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ያለውን የሰው ኃይል በበጎ ፍቃድ በማደራጀት ድህነትን በሚቀንሱ፣ ምርታማነትን በሚጨምሩ፣ አካባቢን በሚጠብቁ መስኮች ላይ በማሰማራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የጋራ ግቦችን ለማሳካት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ረገድ እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት በሀገር ዉስጥ በጎ ፍቃደኞችን በማደራጀት፣ ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች እና ህጻናት ሥነ ልቦና መገንባት እና ማቋቋም፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አዛውንቶችን መንከባከብ ጨምሮ ሌሎችም ተግባራት ይበል የሚያሰኙ ናቸው እና ሊጠናከሩ ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የበለጠ ለሟሟላት ያልተደመጡትን በማዳመጥ፣ ያልታዩትን በማየት እንዲሁም ያልተፈቀዱትን በመፍቀድ ፍትሐዊ እና አካታች ሥርዓት በመከተል በዘላቂ ልማት እና መፍትሔ ላይ ማተኮር የሁሉም ችግሮቻችን መፍቻ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
