
አዲስ አበባ ፡ ግንቦት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባንኩ ለሦስት ወራት ሲያካሄድ የቆየውን ሰባተኛውን ዙር በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ደንበኞች ይቆጥቡ ይሸለሙ መርኃ ግብር ሲያጠናቅቅ ያዘጋጀውን ሽልማት ለባለ ዕድለኛ ደንበኞቹ አስረክቧል።
በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው መርኃ ግብር አሸናፊ ለኾኑ ደንበኞቹ፣ የአውቶሞቢል፣ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ፣ ማቀዝቀዣዎች ፣ ዘመናዊ ስልኮች፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች እና የውኃ ማጣሪያ ሽልማቶችን ነው ያስረከበው።
ባንኩ በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያዘጋጀውን 7ኛ ዙር የቁጠባና ሽልማት መርኃ ግብር በማጠናቀቅ የሎተሪ ዕጣዎቹን መጋቢት 30/ 2015 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ በሕዝብ ፊት በይፋ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ባንኩ 11ኛው ዙር የውጪ ምንዛሪ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ መርኃ ግብር በመካሄድ ላይ ሲኾን በቅርቡ ሲጠናቀቅ በብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደር በሚከናወን ይፋዊ ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት አሸናፊዎቹ እንደሚለዩ የቡና ባንክ ማርኬቲንግ እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አባይነህ ሀብቴ ተናግረዋል።
አቶ አባይነህ 8ኛው ዙር በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ደንበኞች ይቆጥቡ ይሸለሙ መርኃ ግብርም በቅርቡ እንደሚጀመር ነው የነገሩን።
ቡና ባንክ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በከፈታቸው 464 በላይ ቅርንጫፎቹ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማፍራት እንደቻለ ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- እዮብ ርስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
