
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት በዘንድሮው የክረምት ወቅት በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑንም አስታውቋል፡፡
የውብ ተፈጥሮ ባለቤት፣ የብርቅዬ እንስሳት መገኛ የኾነው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛው ሥፍራ እንደኾነ ይነገራል፡፡ የራስ ደጀን ውብ ተራራዎች፣ የበርካታ ፏፏቴዎች መገኛ ስሜን፣ ድንቅ ውበት ካላቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ከግንባር ቀደምቶቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ ይህን ውብ እና ተናፋቂ ሥፍራ የበለጠ በአረንጓዴ ለመሸፈን ሀገር በቀል ችግኞች እየተተከሉበት ነው፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዛናው ከፍያለው በፓርኩ ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከሉ 25 ሺህ 105 ችግኞች መካከል 94 በመቶ የሚኾኑት ጸድቀዋል ነው ያሉት፡፡
94 በመቶ የሚኾነው ችግኝ እንዲጸድቅ ምክንያቱ ደግሞ ችግኞችን የሚንከባከብና የሚጠብቅ ሰው በመሠማራቱ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለተተከሉት ችግኞች ልዩ እንክብካቤ እና ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሠራባቸውም ገልጸዋል፡፡ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተባበሩ እየሠሩ መኾናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ዓመት 50 ሺህ ችግኞችን በ10ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ማቀዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ችግኞች የሚተከሉበትን ቦታ የመለየትና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ወይራ፣ የሀበሻ ጽድና ሌሎች ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉም ተናግረዋል፡፡
412 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ወይም 441 ሺህ 200 ሄክታር ስፋት ያለው ፓርኩ 20 በመቶው በደን የተሸፈነ ነውም ብለዋል፡፡ የፓርኩን አብዛኛውን ክፍል በደን ለመሸፈን ብዙ ሥራዎች እንደሚጠይቁም ነው ያብራሩት፡፡ በየጊዜው በፓርኩ ቃጠሎዎች እንደሚነሱ ያስታወሱት ኀላፊው ጉዳቱን ለመቀነስ እና ጉዳት የሚደርስበትን የፓርኩን ክፍል እንዲያገግም ለማድረግ ችግኝ መትከል አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
