“በክልሉ በክረምት ወቅት ለመትከል ዝግጁ የኾነ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

104

ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለተከላ ከተዘጋጁት ውስጥ ከ3 መቶ ሺህ በላይ ችግኞ ሀገር በቀል መኾናቸው ተመላክቷል። በአማራ ክልል የተራቆቱ አካባቢዎችን በሥነ ሕይታዊ ዘዴ የመሸፈን ልምድ እያደገ መጥቷል።

በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ። በተደጋጋሚ በእርሻ፣ በጎርፍ እና በነፋስ አማካኝነት አገልግሎት የማይሠጡ አካባቢዎች አገግመው ወደ ምርት ተመልሰዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የደን ባለሙያ ባንቺአምላክ ሞላ በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ባለሙያዋ ከተዘጋጁት ሀገር በቀል ችግኞች ውስጥ ፅድ፣ ዋንዛ፣ ብሳና፣ ወይራ፣ የሀበሻ ፅድ የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።

ወይዘሮ ባንቺአምላክ ከውጭ ሀገር ዝርያዎች ውስጥ ባሕርዛፍ፣ ዲከረንስ፣ ግራቢሊያ ፣የፈረንጅ ፅድ እና ሳስፓኒያ ትልቁን ቁጥር እንደሚይዙ ነው የተናገሩት።

የተዘጋጁት ችግኞች ከ192 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚተከሉ ሲኾን በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 ሚሊዮን በላይ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ነው ያነሱት።

የተዘጋጁ ችግኞች በአብዛኛው በወል መሬት ላይ የሚተከሉ ሲኾን ቀሪው በአርሶ አደሮች ማሳ የሚተከል ይኾናል ብለዋል።

አርሶ አደሮች ችግኞችን ወስደው የመትከል እና ተንከባክቦ ጥቅም እንዲሠጡ የማድረግ ሥራውን ከዓመት ዓመት አጠናክረው ቀጥለውበታል ነው ያሉት ባለሙያዋ።

የቅድመ ዝግጅት አፈጻጸሙ ከዞን ዞን የተለያየ ይሁን እንጂ ጅማሮው በሁሉም አካባቢ በእኔነት ስሜት እየተተገበረ መኾኑን ወይዘሮ ባንቺአምላክ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም
Next articleበስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከተተከሉት ችግኞች መካከል 94 በመቶ መጽደቃቸውን ጽሕፈት ቤቱ አስታወቀ፡፡