
ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በርካቶቹ የዓለም ሀገራት የሥነ-መንግሥት ቅርጽ እና ሥርዓት ሳይኖራቸው ኢትዮጵያ ግን የጸና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት የመሰረተች ጥንታዊት ሀገር ናት፡፡ ከሕገ ልቦና እስከ ሕገ ልዕልና፤ ከዘውዳዊ ሥርዓት እስከ ዘመናዊ መንግሥት የካበተ ልምድ፣ የተፈተነ ብቃት እና የተከፈለ መስዋዕትነት ያካበተች ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
ኢትዮጵያ የተሰደዱትን ተቀብላ፤ የተጋጩትን አሸማግላ ለዓለም ሠላም ብዙ ሠርታለች፡፡ የተበተኑትን አሰባስባ፣ የተጨቆኑትን አጠናክራ፣ የተለያዩትን አገናኝታ እና የፈረሰውን ገንብታ ጽኑ ሀገር ብቻ ሳይኾን ጠንካራ አህጉርም እንደመሰረተች የግንቦት ወር አንዱ ምስክር ነው፡፡ የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ከስድስት አሥርት ዓመታት በፊት ግንቦት 16/1956 ዓ.ም ላይ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አፍሪካ ከሞኖሮቪያ እስከ ካዛብላንካ የጥል ግድግዳ እና የልዩነት መንገድ የለያያቸውን ወንድምአማቾች በእርቅ እና ሽምግልና ድልድይ ሠርታ ያገናኘች የአህጉሪቷ መርከብ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ከሊቢያ እስከ ኮሪያ ሠላም አስከባሪዎቿን አሰማርታ ለዓለም ሠላም ዘብ ቆማለች፡፡ ለዘመናት ነጻነቷን አስጠብቃ ለሌሎች ሀገራት የባርነት እና የጭቆና ቀምበር መሰበር ምክንያትም ኾናለች፡፡
“በሕግ አምላክ” ስለተባሉ ብቻ ለሕግ ልዕልና ፍጹም ታማኝነት እና ትህትና ተፈጥሯዊ መለያቸው የኾኑት ኢትዮጵያዊያን በተለይም ከዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ትውውቅ በኋላ ለሌሎች የሚተርፈው የመከባበር እና የወንድማማችነት እሴት በብዙው ሲሸረሸር ይስተዋላል የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ በየዘመኑ የራሳቸውን በጎ አሻራ አሳርፈው ያለፉ ነገሥታት እና መንግሥታት አሉ፡፡
ነገር ግን ሁሉንም በአንድ የሚያስማማ እና ቅሬታን ያነጠፈ የሀገረ-መንግሥት ታሪክ በዓለም ላይ ታይቶ አይታወቅም የሚሉት የደኅንነት ጥናት ተቋም የሥነ-ልቦና አማካሪ ወይዘሮ ሰብለ ኃይሌ በኢትዮጵያም በየዘመኑ በነበሩ ሥርዓቶች የተፈጠሩ ቅራኔዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል ይላሉ፡፡ በየዘመኑ የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ቅራኔዎች ውለው ሲያድሩ የሥርዓቱ ደጋፊዎች እና ነቃፊዎች በኾኑ ቡድኖች መካከል ቁርሾ መኖሩ ተፈጥሯዊ የአስተዳደር ክስተት ነው፡፡
በየወቅቱ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ስብራቶች የፈጠሩትን ቅሬታ እና የታሪክ አረዳድ ለማረም ከመደበኛው የሕግ እና የዳኝነት ሥርዓት የራቀ አሠራርን ይጠይቃል ያሉት አማካሪዋ በሽግግር ፍትህ እና መሰል ተጓዳኝ የምክክር እና የግልግል ሥርዓት ቅራኔዎችን በመፍታት ዘላቂ ሠላም እና መረጋጋትን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል ነው ያሉት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሀገራዊ ቁርሾዎችን በምክክር ለማረም እና ለመፍታት ጥረት ተደርጎ ነበር ያሉት አማካሪዋ ሁሉን አቀፍ፣ አሳታፊ እና ከቡድን ፍላጎት ነጻ ባለመኾናቸው የሚጠበቀውን ያክል ለውጥ አምጥተዋል ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡
“ሥብራቶቻችን ተፈጥሯዊ ሳይኾኑ ሰው ሰራሽ ናቸውና መታከም ይችላሉ” ያሉት ወይዘሮ ሰብለ ሁሉን አሳታፊ፣ ሀገራዊ አንድነትን ያስቀደመ እና ዘላቂ ሠላምን የሚያመጣ እውነተኛ ምክክር ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ሠላም የሚጀምረው በሰዎች አዕምሮ ውስጥ በመኾኑ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን ግለሰባዊ ጥረት፣ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የገጠሟት ፈተናዎች ከኢትዮጵያዊያን አቅም በታች በመኾናቸው ለሀገራዊ ሠላም እና አንድነት ከግማሽ በላይ መንገድ መጓዝ የዜጎች የዜግነት ግዴታ ተደርጎ መቆጠር አለበትም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
