“የኢትዮጵያ መዳኛ ትርክት አብሮነት፣ ወንድማማችነትና በጋራ ሀገርን የመገንባት ትርክት ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

165
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ)
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ በክልሉ የሚገኙ የዞንና የከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ ውይይት በባሕር ዳር ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ቀውስ የአመራር መናጋትን ይፈጥራል፤ በዚህ ምክንያት የመልካም አስተዳር ችግሮችን የሚያባብስ እና የአካባቢን ሠላም የሚያደፈርስ በመሆኑ ለዚህ የሚመጥን የሚዲያና የተግባቦት ሥራ በሁሉም አካባቢዎች በአግባቡ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በሀገራችንም ሆነ በክልሉ ብዙ አይነት የትርክት መዛነፍ እንዳለ ያነሱት ቢሮ ኃላፊው፤ ሀገርን ሊያድን የሚችለውን ትርክት ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡
“የኢትዮጵያ መዳኛ ትርክት አብሮነት፣ ወንድማማችነትና በጋራ ሀገርን የመገንባት፣ ኢኮኖሚን የማሳደግ ትርክት ነው” ያሉት አቶ ግዛቸው ከዚህ ውጪ ያሉ ትርክቶች ሀገርን የሚያፈርሱና ለጠላት አጋልጠው የሚሰጡ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት አድርጎ የተግባቦት ሥራ አለመሥራት በኮሙኒኬሽን መዋቅሩ የሚታይ የተግባቦት ዝንፈት መሆኑን የገለጹት ቢሮ ኃፊው የአብሮነት እሳቤዎችን በሚያጎሉ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ለሕዝቡ መድረስ የሚገባውን ወቅታዊ መረጃ ተግባቦትን በሚያጠናክር መልኩ ሁሉንም የመገናኛ አማራጮች በመጠቀም የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleቺርቤዋ ጉንቤት 15 ጌርክ 2015 ምሬት አሜታ /አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን/
Next article“ሥብራቶቻችን ተፈጥሯዊ ሳይኾኑ ሰው ሰራሽ ናቸውና መታከም ይችላሉ” የደኅንነት ጥናት ተቋም የሥነ-ልቦና አማካሪ ወይዘሮ ሰብለ ኃይሌ