
መሁባ ጋሻው ግንቦት ሁለት ቀን 2011 ዓ.ም የወይዘሮ ዚነት ጌቱ ልጅ መታመሟን ተከትሎና እናት ልጇን ለማሳከም አቅም የሌላት መሆኑን በመገንዘብ “እኔ እረዳሻለሁ” በማለት ከሐይቅ ከተማ ወደ ደሴ መጥታ እንድትተከም በማሳመን እንድትሄድ አድርጋታለች።
ደሴ ከተማ የሚገኝ የግል ጤና ተቋም ገብተው ሕጻኗ ምርመራ እንዲደረግላት አብራት በመሆን ስታግዛት ከቆየች በኋላ የሕጻኗ እናት የልጇን የምርመራ ውጤት ለማምጣት ስትገባ ተከሳሿ በጊዜው የዘጠኝ ወር ጨቅላ የነበረችውን ሕጻን ይዛ ተሰውራለች፡፡
እናት ዚነት የልጇን የምርመራ ውጤት ይዛ ስትመለስ ልጇንና ስትረዳት የነበረችውን ሴት ከቦታቸው ስታጣቸው ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ በመግባት ለደሴ ከተማ ፓሊስ ጉዳዩን አሳወቀች፡፡ የከተማው ፖሊስም የተጠርጣሪዋን አድራሻ ለማግኘት ማፈላለጉን ቀጠለ፡፡ በፍለጋው ሂደትም ተከሳሿ ቦርሳዋን ጥላ በመሄዷና በቦርሳዋ ውስጥ ደግሞ ሞባይሏን ሞልታ የጣለችውን የሞባይል ካርድ መነሻ በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ተከሳሿ አፋር ክልል ዱለቻ የተባለ ስፍራ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሏን አብመድ ዘግቦ ነበር፡፡
ግለሰቧ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላም ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ከፍቶ ምርመራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ መርቷል፡፡ የደሴ ከተማ ዐቃቤ ሕግም በግለሰቧ ላይ ክስ መስርቶ ሲከራከር ቆይቷል፡፡ ተከሳሿ ፍርድ ቤት ቀርባ የተከሰሰችበት ወንጀል ተነብቦላት የእምነት ክህደት ቃሏን እንድትሰጥ ስትጠየቅ ክዳ ተከራክራለች፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና ሰነድ ማስረጃ መርምሮ ግለሰቧ ጥፋተኛ መሆኗን በይኗል፡፡ በመሆኑም የደሴ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ሕዳር 11 ቀን 2012ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሿን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል በማለት ወንጀለኛዋ በ16 ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ወስኗል።
ዘጋቢ፦ አሊ ይመር- ከደሴ