በበአማራ ክልል በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ወጣቶች መሳተፋቸው ተገለጸ ፡፡

141

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ተሳታፊ መኾናቸውን የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

ላለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በነበረው የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚዎች ኾነዋል ተብሏል፡፡

ሀገር ተረካቢ ወጣቶች አካባቢያቸውን እና ሀገራቸውን በውል ከሚረዱባቸው፣ አገልግሎት መስጠትን ከሚለማመዱባቸው እና ኅላፊነት መቀበልን ከሚጀምሩባቸው የተግባር ስምሪት መካከል አንዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜ እና አፈጻጸም ቢኖረውም መሠረታዊ እሳቤው ግን ወጣቶችን ከማኅበረሰቡ ጋር ማስተዋወቅ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተዘወተረ የመጣው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለበርካታ ዜጎች ከሰጠው ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ በዘለለ ወጣቶች ማኅበረሰቡን እንዲረዱ አግዟል ያሉት የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አቶ ተሾመ ፈንታው ናቸው፡፡ ምክትል ቢሮ ኅላፊው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት እያገኘ መጥቷል ይላሉ፡፡

በ2015 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል ያሉት አቶ ተሾመ፤ ባለፉት ስምንት ወራት በነበረው የወጣቶች የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን የክልሉ ዜጎች ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል፡፡ የአረጋዊያን እና የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ጥገና እና እድሳት፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ ተፈናቃዮችን መደገፍ እና ማቋቋም፣ የጤና፣ ትምህርት እና ማኅበረሰብ አቀፍ የጸጥታ አገልግሎት በወጣቶቹ የተሰጡ አገልግሎቶች ናቸው ብለዋል፡፡ በበጋ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገለግሎት 285 ቤቶች በአዲስ ተገንብተዋል፤ 503 ቤቶች ደግሞ ተጠግነዋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው በወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ከምንም በላይ ግን ሀገር ተረካቢ ወጣቶች አገልጋይነትን ተምረውበታል ተብሏል፡፡

በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳተፉ እና ያስተባበሩ ወጣቶችን ያመሰገኑት ምክትል ቢሮ ኅላፊው አገልግሎቱ ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል ብለዋል፡፡ ከአንድ ወር በኋላም የ2015 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብርን በምስጋና ተዘግቶ የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብርን በይፋ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ምክትል ቢሮ ኅላፊ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በአሲድ የተጠቃን ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኖራ አክሞ ምርታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
Next article62 በመቶ የክልሉ ወጣቶች በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሳተፉ ተገለጸ፡፡