በአማራ ክልል በአሲድ የተጠቃን ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኖራ አክሞ ምርታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

71

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት በአሲድ የተጠቃን 12 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በኖራ በማከም ምርታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ለእርሻ ከሚውለው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታሩ በአሲድ መጠቃቱ በጥናት ተረጋግጧል።

የአሲዳማ ችግር በሁሉም አካባቢዎች ቢስተዋልም በተለይ ከፍተኛ የዝናብ ፍሰት ባለባቸውና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይ ገልጸው፤ “ለዚህም ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ይጠቀሳሉ” ብለዋል።

የመሬቱን የአፈር ለምነት ወደነበረበት ለመመለስ የተፈጥሮ ማዳበሪያና ኖራን ጨምሮ ሌሎች ለአፈር ለምነት መሻሻል የሚያግዙ ንጥረ ነገሮችን አርሶ አደሩ በስፋት እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመንም ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ በመጠቀም 12 ሺህ 500 ሄክታር በአሲድ የተጠቃን መሬት ለማከም ለአርሶ አደሩ ኖራ የማቅረብ ሥራ መጀመሩንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የደጀን ኖራ ማምረቻ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው “እስካሁንም ከ7 ሺህ 800 ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ እየተሰራጨ ይገኛል” ብለዋል።

አቶ አግደው እንዳሉት በአሲድ የተጠቃን መሬት በአማካኝ በሄክታር 20 ኩንታል ኖራን ተጠቅሞ ማልማት ከተቻለ እስከ 34 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት ይቻላል።

በአዊ ዞን የባንጃ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የአፈር ለምነት ባለሙያ ወይዘሮ ቤተልሔም ገነት በበኩላቸው፣ አብዛኛው የወረዳው ቀበሌ ደጋማና ዝናብ የማይለየው በመሆኑ መሬቱ በአሲድ የተጠቃ ነው።

ዘንድሮ 232 ሄክታር በአሲድ የተጠቃ የእርሻ መሬትን ከ1 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በኖራ አክመው እንዲያለሙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም መሬቱን ለማልማትም 4ሺህ 640 ኩንታል የኖራ ምርት ከደጀን ኖራ ፋብሪካ በማስመጣት ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን አመልክትዋል።

በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን በኖራ አክመው ማልማት ከጀመሩ ወዲህ በሩብ ሄክታር እስከ 10 ኩንታል የስንዴና የገብስ ምርት ማግኘት እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደሳለው በላቸው ናቸው።

በመጪው የመኸር ወቅትም ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በኖራ አክመው በስንዴ ለማልማት አንድ ኩንታል ተኩል ኖራ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ተጨማሪ ኖራም ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት 3ሺህ 390 ሄክታር መሬት በአሲድ የተጠቃን መሬት በኖራ አክሞ በስንዴ፣ በገብስና በሌሎች ሰብሎች ማልማት ተችሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት የተቋማት አፈጻጸም ግምገማ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የምክር ቤት አባላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
Next articleበበአማራ ክልል በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ወጣቶች መሳተፋቸው ተገለጸ ፡፡