
ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የተቋማት አፈጻጸም ግምገማ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም መገምገሙ ይታወቃል።
በመድረኩ የዘጠኝ ወር የማክሮ ኢኮኖሚውን እና የሴክተሮች ልዩ አፈጻጸም ተገምግሟል።
የሚኒስትሮች የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጡም ይታወቃል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ የሚኒስትር ዴኤታዎችና የተቋማት የዘርፍ አፈጻጸም እየተገመገመ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት የማክሮ ኢኮኖሚው አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በየዘርፎቹ በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችል አመላካች ውጤት መኖሩን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
በዚህ መድረክ በስድስት ወራት ግምገማ ወቅት የተቀመጡ አፈጻጸሞች ግምገማ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም እንደሚገመገም፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ ተናግረዋል።
በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና ቋሚ የኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የተቋማት ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
መድረኩ ነገም የሚቀጥል ሲሆን በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ የሚመክር ይሆናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
