ኢትዮጵያ ታኅሳስ 07 ቀን 2012ዓ.ም ሳተላይት ልታመጥቅ ነው፡፡

236

ኢትዮጵያ ታኅሳስ 07 ቀን 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡21 ላይ 72 ኪሎ ግራም የምትመዝን የ‹ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት› ልታመትቅ ነው፡፡ ሳተላይቷ ከመሬት 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትቀመጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይዝርዝር መግለጫ እየሰጠ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በኋላ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ልታመጥቅ መሆኑን ሐምሌ 25 ቀን 2011ዓ.ም ዘግበን እንደነበር ይወሳል፡፡

በመሬት ያሉ ነገሮችን እና ስለመሬት መረጃ የምታሰባስብ በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ሀገራት ምሁራን የተሠራች ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነበር የዘገብነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በወቅቱ እንደተናገሩት የመሬት ምልከታ ሳተላይቷን ለማምጠቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ሳተላይቷን ለማምጠቅ የ‹‹ግራውንድ ስቴሽን›› ግንባታውም እንደተጠናቀቀ ዶክተር ሰሎሞን አስታውቀው ነበር። አሁን ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ ከምትገኘው ሳተላይት በኋላ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ያለማንም አጋዥ ራሳቸውን ችለው የሚሰሩበት መንገድ እንደሚፈጠርም ዋና ዳይሬክተሩ መናገራውን በዘገባችን አስነብበን ነበር። ‹‹ሳተላይቷ ወደ ሕዋ የምትመጥቀው ዘርፈ ብዙ ተልኮ ይዛ ነው›› ያሉት ዶክተር ሰለሞን በዋናነት ለእርሻ አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን እና ሰብሎቹን ለመለየት፣ ለአካባቢ እና ለደን ጥበቃ፣ ለውኃ ልማት፣ ለማዕድን ፍለጋ ሥራ እና ለአየር ንብረት ቁጥጥር እና ትንተና የሚያገለግሉ መረጃዎችን እንደምትሰበስብ ገልጸው ነበር፡፡

የሳተላይቷ መቆጣጠሪያ፣ መከታተያ እና ትዕዛዝ መስጫ ጣቢያ እንጦጦ ላይ እንደሚሆንም ዶክተር ሰለሞን መናገራቸው የሚታወስ ነው። ሳተላይቷ የምኅዋር (ፍሪክዌንሲ) ምዝገባ ተደርጎላታል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትተዋወቅም ተደርጓል ነበር የተባለው፡፡ የሳተላይት የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ መጠየቁንና ማምጠቂያ ጣቢያውን የቻይና መንግሥት እንደፈቀደ እንዲሁም በኢትዮጵያ በኩልም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ዘግበን ነበር።

ሳተላይቷ ከባሕር ጠለል በላይ 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ትመጥቃለች። ሳተላይቷ በምድር ምልከታ ላይ ኢትዮጵያ የምታወጣውን ወጪ ከማስቀረትም በላይ ገቢ ታስገኛለች ተብሎ ይጠበቃል። ሳተላይቷ በጣም ዘገየ ቢባል ታህሳስ 2012 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ እንደምትመጥቅም ዶክተር ሰለሞን ለአብመድ አስታውቀው ነበር።

ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ -ከአዲስ አበባ

Previous articleሕጻን የሠረቀችው ግለሰብ በ16 ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት ተቀጣች፡፡
Next articleየጎንደር ከተማ አስተዳድር ከእቅዱ በላይ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን አስታውቋል፡፡