
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሥራና ሥልጠና፣ ገቢዎች እንዲሁም የንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች በክልል ደረጃ በቀጣይ ወራት በትኩረት ሊሰሩ የታቀዱ ሥራዎችን አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የስራ ዕድል ፈጠራ ሥራና የዋጋ ንረትን ማሻሻል ልዩ ትኩረት የሚሹ አጀንዳዎቻችን በመኾናቸው ውጤታማ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በጥብቅ ቅንጅት ይሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀምበሬ (ዶ.ር) በበኩላቸው የሥራ ዕድል ፈጠራና የዋጋ ንረት ላይ የምንሠራውን ሥራ በየጊዜው እየገመገምንና የሚያጋጥሙንን ችግሮች እየፈታን ልንሠራ ይገባል ብለዋል። አጀንዳዎችን የህልውና ጉዳይ አድርገን እንሰራለንም ሲሉ ገልፀዋል። በተጨማሪም አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ህገ ወጥ የንግድ ተዋንያን ተግባራትን ተከታትሎ የማስተካከል ስራ በቀጣይነት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የስራ ዕድል ፈጠራ ስራን በዕቅዳችን ልክ ለመከወን፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እና ፍትሃዊነትን የተላበሰ የንግድ ስርዓት እንዲኖረን ለማስቻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 
በየደረጃው ያለው አመራር የተሰጠውን እያንዳንዱን ተግባር ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እየተወያየ በማያቋርጥ ትጋት ሰርቶ ውጤታማ ሊያደርግ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አመራሮች በቀጣይ ሊከወኑ ይገባል ተብለው የተቀመጡ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		