“ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች”

110

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ክፋትና ምቀኝነት የሌለባት፣ መሳደድና መንገላታት የማይኖርባት፣ ሰላም እንደ አፍላግ የሚመነጭባት፣ እንደ ውቅያኖስ ሰፍቶ የሚኖርባት፣ እንደ ለምለም መስክ የተዋበባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፣ ደግነትና መልካምነት የበዛባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፡፡

ስሞት አፈር ስሆን የሚባባሉባት፣ ወንድም ለወንድሙ ጋሻ የሚሆንባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፣ ፍቅር እንደ ካባ ያጎናጸፋት፣ ግርማና ውበቷን የገለጠላት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፣ ልጆቿ በፍቅር የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፣ ዘር የማይቆጠርባት፣ አንድ ሠንደቅ ብቻ የሚከበርባት፣ ሠንደቅ ከምንም እና ከማንም በላይ ከፍ ከፍ የሚልባት፣ ከምዕራብ ንፍቅ እስከ ምሥራቅ ንፍቅ፣ ከሰሜን ንፍቅ እስከ ደቡብ ንፍቅ ልጆቿ እንደ አሻቸው የሚንቀሳቀሱባት፣ በአሻቸው ላይ የሚኖሩባት፣ ልጆች ወልደው የሚስሙባት፣ እሸት ቆርጠው የሚቀምሱባት፣ ከላሞቻቸው ወተት የሚጠጡባት፣ የማይሰጉና የማይደናገጡባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፡፡

ያቺ ጠላት ሁሉ እጅ የሚነሳላት፣ ነጻነት የጸናባት፣ ሰላቶና ምቀኛ የማይረማመድባት፣ አንድነት የጠነከረባት፣ ከራስ በላይ ለሀገርና ለሕዝብ ክብር የሚሉ የበዙባት፣ መጠላለፍ እና መደነቃቀፍ የሌለባት፣ ወንድም ከወንደሙ ጋር የሚተማመንባት፣ እናት ከልጆቿ ጋር በፍቅር የምትኖርባት ኢትዮጵያ ትናፍቃለች፡፡ ያቺ ፍቅር የመላባት፣ ብራና እየተፋቀ፣ ቀለም እየተበጠበጠ አኩሪ ታሪክ የሚጻፍባት፣ መተሳሰብ የነገሠባት፣ ከራስ በፊት ለሀገርና ለሠንደቅ የሚወደቅባት ኢትዮጵያ ትናፍቃለች፡፡

ዘረኝነት የጠፋባት፣ ጎራ ለይቶ መቧቀስ የሌለባት ኢትዮጵያ ትናፍቃለች፡፡ ኢትዮጵያ እየኖሩባት ትናፍቃለች፣ እየኖሩባት ታሳሳለች፣ ለሚወዷት ሁሉ የእርሷ መከፋት ያስለቅሳቸዋል፣ የእርሷ መጨነቅ ያስጨንቃቸዋል፣ የእርሷ መጎሳቆል ያጎሳቁላቸዋል፡፡ የእርሷ መደሰት ያስደስታቸዋል፣ የእርሷ ከፍ ከፍ ማለት ከፍ ያደርጋቸዋል፣ የእርሷ ኃያል መሆን ኃያል ያደርጋቸዋል፣ የእርሷ መኩራት ያኮራቸዋል፡፡ ለሚጠሏት ሣቋ ያስለቅሳቸዋል፣ ደስታዋ ያሳዝናቸዋል፣ እርዛቷ ሀሴትን ይሰጣቸዋል፣ ክብሯ ያበሳጫቸዋል፣ ታላቅነቷ እረፍት ይነሳቸዋል፡፡ ለምን ? እነርሱ ከለቅሶዋ ሳቅ ያተርፋሉ፣ ከሀዘኗ ሠርግ ይፈጥራሉ፣ ከእናቶች እንባ ላይ ወይን ይቀዳሉና፡፡

ዶናልድ ሌቪን በጻፉትና ሚሊዮን ነቅንቅ ወደ አማርኛ በመለሱት ትልቋ ኢትዮጵያ የብዙ ነገዶች ማኅበረሰብ በተሰኘው መጽሐፍ ስለ ኢትዮጵያን ሲገልጹ “ የትልቋ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የተለያዩ ባሕል ፈጥረው፣ በልዩ ልዩ ጎሳ ተከፋፍለው፣ ለየብቻቸው ተፈናጥረው፣ ተገንጥለውና ተሸሽገው አልኖሩም፡፡ በሺህ ዘመናት ታሪካቸው ሲገናኙ በአንድ ላይ ኖረዋል፡፡ የትልቋ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት አብረው የኖሩት እርስ በእርሳቸው በዘረጉት የድር መረብ ነው፡፡ አንዳንዴ መንማናና ጠባብ ሲሆን፣ አንዳንዴ ሰፊና ጥልቅ የሆነ፣ ከቶም ሁልጊዜ የነበረና ያልጠፋ በመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ የጀርባ አጥንት የሆነው እንደዚህ አይነቱ መረብ ነው” ብለዋል፡፡

የመተሳሰሪያ መረባቸው አይቆረጥም፣ እንዳስተሳሰራቸው፣ በአንድነት እንዳቆማቸው ኖሯል፣ ይኖራል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጥልቅና ረጅም በሆነው ታሪካቸው እልፍ የመተሳሰሪያ እና የአንድነት ገመዶችን ፈጥረዋል፡፡ በአንድነት የመሰባሰቢያቸው እና መገናኛቸው ደግሞ በሰማይም በምድርም በክብር ስትውለበለብ የምትታየው ሠንደቃቸው እና ነጻነትን ያጸናቸው ኢትዮጵያ ሀገራቸው፣ መከራ የሚያጠነክረው ኢትዮጵያዊነታቸው ነው፡፡ መከራዎች ቢበዙም፣ ፈተናዎች ቢያይሉም፣ ሞትና መሳደድ ቢሰፋም ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊነት ዝቅ ሳይሉ ኀያል ታሪክ ጽፈዋል፣ ታላቅ ሀገር አቆይተዋል፡፡ የእነርሱ መገለጫቸውና ልካቸውም ጽኑ ኢትዮጵያዊነት እና ከፍታ ነው፡፡

አሁን አሁን ለዘመናት ተሳስረው የቆዩበት ድራቸው ፈተና እየበዛበት፣ ምድሯም ችግር እየበረከተባት ሄዳለች፡፡ የፈተናዎቿና የችግሮቿ መበራከትና መብዛትም ዋጋ አስከፍለዋታል፣ አቁስለዋታል፡፡
በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ጠና ደዎ (ዶ.ር) ፈተናዎች የበዙባት ኢትዮጵያ ፈተናዎቿ አልፈውላት ሰላማዊ ስትሆን እናፍቃታለሁ ይሏታል፡፡ ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ፣ የናፍቆቴን ያክል አይቼ መጠግብ ስለማልችል ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች ይላሉ ዶክተር ጠና፡፡ ሀገር የጋራችን ናት፣ በጋራ ካልሠራንላት እና ካልሠራንባት ሀገር ሀገር አትሆንም፡፡ እንደናፈቅኋት ልለያት ነው ወይ? የሚል ስሜት አለብኝ ነው ያሉኝ፡፡

እያንዳንዳችን የናፍቆት ስሜት ካለን፣ የምንናፍቃትን፣ የምንወዳትን፣ የምናከብራትን ሀገር ሳናያት እንዳንለያት ተናፋቂዋን ሀገር መፍጠር አንችልም ወይ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡
እሳቸው የሚናፍቋት ታላቋን፣ ሰላማዊቷን፣ ልጆቿ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባትን፣ መጠላለፍ የሌለባትን፣ አንደኛው በአንደኛው ላይ የማይዘምትባትን፣ በአንደኛው እንባና መከራ ሌላኛው ሠርግ የማይሠረግባትን ብሩህና ውብ የሆነችው ኢትዮጵያን ነው፡፡ ያቺን ልጆቿ የማያለቅሱባትን፣ ቁስል ያልበዛባትን፣ እንግልትና መከራ ያልበዛባትን ኢትዮጵያን ይናፍቋታል፡፡

ተነጋግረን ተናፋቂዋን ሀገር ማምጣት አንችልም ወይ? እያሉ የሚጠይቁት የፍልስፍና መምህሩ መነጋገር ነው የምንናፍቃትን ሀገር የሚያመጣት፣ ዱላ ተናፋቂዋን ሀገር አላመጣልንም፣ ዱላ ቁስላችን እና ድህነታችንን እያሰፋ ሄደ እንጂ ችግራችንን አልፈታልንም ይላሉ፡፡ መነጋገር ሰፊ አጀንዳ መኾን አለበት፣ በርቀት ማዬት መቻል አለብን፣ በጥልቀት መረዳት ይጠይቃል፣ መልካም ነገሮችን አስፍተን ማዬት አለብን ነው ያሉኝ፡፡

ዶክተር ጠና ልባቸው ትነካለች፣ አብዝታም ትጨነቃለች፣ “እኛ ተናፋቂዋ ኢትዮጵያ ትቅርብን፣ እየቀረችብንም ነው፣ ባይኾን ለልጆቻችን ተናፋቂዋን ኢትዮጵያን ለማስረከብ መሠረት መጣል አለብን” ነው ያሉኝ፡፡ ለምን በእጃችን ያለች ሀገር ትናፍቀናለች? ይላሉ ዶክተር ጠና፡፡

ሁልጊዜም የእርሷ ናፍቆት ያስቸግራቸዋል፣ ተናፋቂዋ የኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳስባቸዋልና፡፡ “ሳናገኛት፣ ሳንረዳት፣ ሳንሆንላት፣ ሳትሆንልን ከምንለያይ ቢያንስ መሠረት ጥለን ማለፍ አለብን” ነው የሚሉት፡፡
ኢትዮጵያ ከእኛ በቀር ማን ሊመጣላት ነው? ማንን ነው የምንጠብቀው? መቼ ? ለምን? ምን አነሰን እኛ ? እያልን መጠየቅ፣ መወያዬት እና መሠረት መጣል አለብንም ብለዋል፡፡ ሀገር እያንዳንዱ ሰው በሚያዋጣው ድርሻ ነው የምትድነው፣ ሌላ ታዕምር የለም፡፡ ትኩረት ማጣታችን፣ አዕምሯችን አለመጠቀማችን ወደ ጸብ ይመራናልም ብለውኛል፡፡

በእጁ ያለችው ኢትዮጵያ የምትናፍቀው፣ ሰላሟና ክብሯ የሚያሳስበው ለክብሯ እና ለፍቅሯ ይሠራ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡ የናፈቃትን ሀገሩን ይኖርባት፣ የሚመኛትን ሀገሩን ያገኛት ዘንድ በአንድነት እንዳጸኗት፣ በክብር እንዳቆዩት፣ መቁሰሏን እንደ ቆሰሉላት፣ መድማቷን እንደደሙላት፣ ሁሉንም እንደሰጧት እንደ የቁርጥ ቀን ልጆቿ መኾን ያስፈልጋል፡፡ አንድ ከኾኑላት፣ ጥልን እየጣሉ ፍቅርን ካጸኑላት ያን ጊዜ ተናፋቂዋ ኢትዮጵያ ትመጣለች፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመስኖ ከለማው ስንዴ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ያህሉ ምርት ተሰብስቧል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
Next article“የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራን በዕቅዳችን ልክ ለመከወን፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እና ፍትሐዊነት የተላበሰ የንግድ ሥርዓት እንዲኖረን ለማስቻል በቁርጠኝነት እንሠራለን!”የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ