
የጎንደር ከተማ አስተዳድር ከእቅዱ በላይ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከተማ አስተዳድሩ በዚህ ዓመት ለ11 ባለኮከብ ሆቴሎች ፈቃድ ሊሰጥ መሆኑንም ገልጧል፡፡
በከተማዋ ከ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ደግሞ የዕድገታቸውን መለኪያ የሥራ ዕድል ፈጠራ አድርገዋል፡፡
የኢንዱስትሪው እና የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የሥራ ዕድል እና የገበያ ትስስር በመፍጠር ለከተሞች እድገት የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል፡፡ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የተገነቡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከጎንደር ከተማ አቅም እና ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፍላጎት አንጻር ሲታይ ብዙ አለመጣጣሞች እንዳሉ የከተማው ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ተናግሯል፡፡
የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የጎንደር ከተማ ኢንቨስትመንት ተደራሽነትን ከሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አንፃር ተዟዙሮ ቃኝቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በ452 ሚሊዮን ብር የተገነባው ዓባይ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ አንዱ ነው፤ ድርጅቱ ለሠራተኞች ሙሉ የልብስ ስፌት ስልጠና በመስጠት የምርት ሠራ ጀምሯል፡፡ በቀን እስከ 4 ሺህ አምስት መቶ ልብሶችን ያመርታል፡፡ በጊዜያዊ እና በቋሚ 500 ሠራተኞች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል የቴክኒክና ሙያ ምሩቋ ሄለን መኮንን አንዷ ነች፡፡ ሄለን በፋብሪካው ስትቀጠር ሙሉ የሙያ ስልጠና ተሰጥቷት መሠማራቷንና የራሷ ገቢ የምታገኝበት ዕድል እንደተፈጠረላት ተናግራለች፡፡ ድርጅቱ ከማሰልጠን ጀምሮ ሙሉ የሙያ ባለቤት የሚያደርግ በመሆኑ የምታገኛቸውን ልምዶች በመጠቀም ወደፊት በዘርፉ በግሏ ተሰማርታ እንድትሠራ የራስ መተማመኗን እንደጨመረላትም ገልጻለች፡፡
ሌላኛው የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ኢሊ ሳሙና ፋብሪካ ነው፡፡ ከስድስት ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ባለሀብቶች የዞረ የግል ተቋም ነው፡፡ ከዚህ በፊት በ35 ሠራተኞች ተገድቦ የነበረው ሥራ በኢትዮጵያውያኑ ባለሀብቶች እጅ ከገባ በኋላ ሥራውን በማስፋት ከ120 በላይ ቋሚና ጊዚያዊ ሠራተኞችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በቅርብ ወራት ውስጥ ፈረቃውን በማሳደግ የሥራ ዕድሉን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሆነም የተቋሙ ተወካይ ተጠሪ እና የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም አዲሴ አስታውቀዋል፡፡ ፋብሪካው በቀን 200 ካርቶን የልብስ እና 1 ሺህ 200 ካርቶን የገላ ሳሙና ያመርታል፡፡ ከምርት እስከገበያ ድረስ ከሕብረተሰቡ ጋር የተሳሳረ በመሆኑም ፋብሪካው በቀጣይ በሁለት ፈረቃ ሲሠራ ለአካባቢው የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እየሠሩ መሆኑን ነው አቶ ፍቅረማርያም የጠቆሙት፡፡
የጎንደር ከተማን የዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ምቹነት ለማረጋገጥ ከሚረዱ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መካከል በ170 ሚሊዮን ብር ገዳማ የተሠራው የጎንደር ‹ኒልስ ሪዞርት› (ጃካራንዳ ሪዞርት) ተጠቃሽ ኢንቨስተመንት ነው፡፡ ሪዞሪቱ በጊዜያዊ እና ቋሚ ለ110 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከእነዚህም መካከል በሪዞርቱ ግንባታ ከዘበኝነት ጀምረው አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ የውስጥ ውበት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌጡ ታሪክ ይገኙበታል፡፡ አቶ ጌጡ ‹‹የሆቴል ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ኃይል ናቸው›› ብለዋል፡፡ መሰል የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች ዳቦ ከመሆን ባሻገር ዘላቂ የኑሮ መሠረት መሆናቸውን ያረጋግጣሉ እንደሚችሉም ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳድሩ በ2012 በጀት ዓመት ለሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያዘጋጀው መሬት እንደሌለ ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡ በከተማዋ በኢንቨስትመንት ለመሠማራት ዘንድሮ ብቻ ከ120 በላይ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳድር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተጠሪ አቶ ንጉሥ ክብረት ከአስርት ዓመታት በፊት በጎንደር ከተማ ሦስት ኢንዱስትሪዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ወቅት በጎንደር ከተማ ውስጥ በሚገኙ አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች ብቻ 174 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 46 ግንባታ ያጠናቀቁ እና ሥራ የጀመሩ ናቸው፡፡
በከተማዋ ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጭ በማኅበራዊ ዘርፎች 11 ፋብሪካዎች፣ 15 የትምህርት እና የጤና ተቋማት እና 127 የሆቴልና የቱሪዝሞ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 35ቱ በግንባታ ላይ ሲሆኑ ሌሎች ተጠናቀው ሥራ ያልጀመሩትን ጨምሮ 64 የሚሆኑት ባለኮከብ ሆቴሎች መሆናቸውን ባለሙያው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
በጎንደር ከተማ እስከ 2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ድረስ ከ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ1ሺህ 500 በላይ ኢንቨስተሮች በግንባታ፣ በኢንዱስትሪዎች፣ በቱሪዝም እና በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ በዕቅዳቸው መመላከቱን አቶ ንጉሥ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ በየጊዜው የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ጥያቄ ከከተማዋ ዕቅድ ሦስት አራተኛ በላይ እየጨመረ ቢመጣም የመሬት አቅርቦት አለመኖር፣ የቢሮክራሲ መብዛት፣ የኃይል እጥረት፣ የመሠረተ ልማት ችግሮች፣ የውኃ እጥረት ለከተማዋ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ማነቆ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳድር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ደባልቄ ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት እና ወደ ሥራ የማይገቡ ፕሮጀክቶች ለከተማዋ እንቅፋት እንዳይሆኑ ወደ ሥራ ያልገቡ 22 ፕሮጀክቶችን መንጠቃቸውን ተናግረዋል። ‹‹የተነጠቁት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ተደርጎላቸው ዕድሉን መጠቀም ያልቻሉ ናቸው›› ያሉት ኃላፊው ዘርፉን ለማነቃቃት የተነጠቀውን ቦታ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ለሚጠብቁ ባለሀብቶች እንደሚያስተላልፉም አስታውቀዋል። በከተማዋ እስከ ግንባታ ደርሰው ወደሥራ ያልገቡ ባለሀብቶች ለሥራ ዕድል ማነቆ እየሆኑ በመሆኑ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ባልገቡት ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ኃላፊው አስጠንቅቀዋል። የሥራ ዕድል የማይፈጥር ኢንቨስትመንት ላይ እንደማይደራደሩ የተናገሩት አቶ አዲሱ የባለኮከብ ሆቴሎች ቦታ በጨረታ የማስተላለፍ ጥያቄን ለመመለስ ጥናት መደረጉንም ገልፀዋል፡፡
ኃላፊው የመሠረተ ልማት እና የኃይል እጥረቶችን በተመለከተ በባለሀብቶች የሚፈቱትን በጋራ ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረው የኃይል መቆራረጥ እና እጥረትን ግን ለፌዴራል መንግሥት አመልክተው ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ከተማ የባሕልና ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ‹‹ጎንደር የዓለም ዓቀፍ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መዳረሻ እምብርት ናት›› ብለዋል፡፡ ለዚህ የሚመጥን የባለኮከብ ሆቴሎች ተደራሽነት ለመጨመር በዚህ ዓመት ለጠየቁ 11 ባለኮከብ ሪዞርት ኢንቨስትመንቶች ምላሽ ለማሰጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ የትልልቅ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፋብሪካዎች ጋር እኩል በመሆኑ ከዚህ በፊት በዘርፉ ከተፈጠሩ ከ1ሺህ 900 በላይ የሥራ ዕድሎች የሚልቁ ፕሮጀክቶችን እንደሚደግፉም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ግርማ ተጫነ -ከጎንደር