
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ በሕዝብ የተመረጠ ፓርቲ በመኾኑ ለሕዝብ የገባውን ቃል በብቃት መምራትና በውጤታማነት ለመፈጸም አመራሩ መሥራት አለበት ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራህ ተናገሩ።
“ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ መልእክት ሲካሄድ በቆየው ኮንፈረንስ ተገኝተው ከተሳታፊዎች በተነሱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አደም ብልጽግና በፈተናዎች ውስጥ ኾኖ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻለ ፓርቲ መኾኑን ተናግረዋል።
ያሉትን ዕድሎች ወደ ውጤት መቀየር ይገባል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በየደረጃው ያለው አመራር የክልሉን ሕዝብ የሚመጥን ተሻጋሪ የአገልጋይነት ስሜት በመላበስ እና በራስ የመተማመን መንፈስ ይዞ አንድነቱን መጠበቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።
አቶ አደም አያይዘውም እርስ በእርስ መተማመን፣ መርህን ማክበርና መፍትሔ ሰጪ መኾን በየደረጃው ከሚገኝ መሪ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን ለውጡን የሚያስቀጥል መሪ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመጨረሻም የአመራር አንድነት፣ ዲሲፕሊን ማረጋገጥና የሕግ የበላይነት ማስከበር ላይ አመራሩ በልዩ ትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በባሕር ዳር ለቀናት ሲካሄድ የነበረውና የከፍተኛና መካከለኛ መሪዎች የተሳተፉበት ኮንፈረንስ ተጠናቅቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
