
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ የመሪዎች ኮንፈረንስ በልዩ ልዩ ጉዳዮች መክሮ መጠናቀቁ ይታወሳል። የመሪዎች ኮንፈረንስ በመከረባቸው ጉዳዮች ላይ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር)መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የነበረው ኮንፈረንስ በድል ተጠናቅቋል ነው ያሉት። ዓላማውን እና ግቡን በማሳካት በስኬት የተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
ለውስጥ ችግሮቻችን ትኩረት ሰጥተን በዲሞክራሲያዊ ትግል ችግሮችን መፍታት እንዳለብን ተስማምተናል ነው ያሉት። ሕዝብን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ መስማማት ላይ ተደርሷልም ብለዋል። ብልሹ አሠራርን ፣ ሌብነትንና ሕገወጥነትን ሕዝብን በማሳተፍ ማስተካከል እንደሚገባ ምክክር ተደርጎ የጋራ አቋም ተይዟልም ብለዋል።
የውስጥ ችግራችንን ማረም እንደሚገባ መተማመን ላይ ተደርሷል ያሉት ዶክተር ጋሻው የውስጥ ችግሮችን ካረምን የውጫዊ ጫናዎችን መቋቋም እና ፈተናዎችን ማለፍ ይቻላል ነው ያሉት።የውጭ ፈተናዎች በውስጣዊ አንድነት እንደሚፈቱና እንደሚመከቱ መግባባት ላይ ተደርሶ ለተፈፃሚነቱ ይሠራልም ብለዋል።
ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ መሥራት እንደሚገባ በመግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት ዶክተር ጋሻው ኮንፈረንሱ እስከታች ቀጣይነት አለውም ብለዋል። በኮንፈረንሱ ስምምነት ላይ የተረደሰባቸው ጉዳዮች ኅብረተሰቡን ባለቤት ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል።
ክልላዊ አንድነትን በማጠናከር ሕዝቡን የሚመጥን ሥራ መሥራት እንደሚገባ ምክክር እንደተደረገበት ያነሱት ዶክተር ጋሻው የአማራ ክልል እንደ ሀገር ማበርከት የሚገባውን ማበርከት ይገባዋልም ብለዋል። ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል እንደሀገር ማድረግ የሚገባውን እንዲያደርግ አቅም የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
በኮንፈረንሱ ስምምነት የተደረገባቸው ድምዳሜዎች እና አቅጣጫዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ስምሪት መሠጠቱን አስታውቀዋል። ሕዝቡ ለተፈፃሚነቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
