
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊያን በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ደጋግሞ ፈታኝ የህልውና ችግሮች እና አደጋዎች ሲገጥሟቸው ይስተዋላል፡፡
ችግሮቹ ከቅኝ ግዛት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እና የተሳሳተ ትርክት የሚመነጩ ናቸው ተብሎም ይታሰባል፡፡ ወራሪዋ ጣሊያንን ምሥራቅ አፍሪካን በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ጠቅልሎ ለመያዝ ከነበራት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ መንገዷን ጥርጊያ ለማድረግ ከጦሯ በፊት የፕሮፖጋንዳ ክንፏን አስቀድማ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ አሰማራች፡፡
የጣሊያን የፕሮፖጋንዳ ክንፍ ሁለት ዐበይት የጥፋት መርዞችን በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ረጨ፤ ከፋፍሎ መግዛት እና የሐሰት ትርክት፡፡ ጣሊያኖች የክፋት ክራቸውን ሲተረትሩ ዘር፣ ሃይማኖት እና ባሕል ሳይለያያቸው በአንድነት ቆመው ሀገራቸውን ከጠላት፤ ሕዝባቸውን ከውርደት የሚታደጉትን ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን በጎሳ ከፍለው፤ በሃይማኖት ነጣጥለው ለማጥቃት እኩይ ሴራዎችን ጠነሰሱ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ለሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጥላ እና ከለላ ኾኖ ሳለ እውነቱን ገልብጠው አንዱ ለሌላኛው ጠላት ተደርጎ ቀረበ፡፡
ሌላኛው የጥላቻ መርዝ በሐሰት የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ተስሎ እና ተመስሎ ቀረበ፡፡ ኢትዮጵያውያን ረጂም ዘመንን ባስቆጠረው ኑባሬያቸው ጉራማይሌ ታሪክ እና የተለያየ የኑሮ ደረጃ ቢኖራቸውም አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት እና ለመጉዳት የተደራጁበት ወቅት እና ሥርዓት ግን ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እውነታው ይህ ኾኖ እያለ አንዱ ብሔር ሌላኛውን ብሔር፤ አንዱ ሃይማኖት ሌላኛውን ሃይማኖት እንዳሳደደ ተደርጎ ተነገረ፡፡ የጥላቻ መርዙ በወቅቱ ለነበረው የፋሽስት ጣሊያን የወረራ ስልት ብዙም ሠርቷል ባይባልም ውሎ ሲያድር ግን በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ አደጋ መፍጠሩ ግን አይካድም፡፡
ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ነጻነት በኋላ ዘመናዊነት ቀመሱ የምዕራባዊያን አስተሳሰብ እና አስተምህሮ ለዓመታት ተዳፍኖ የኖረውን የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት እንደገና ቀሰቀሰው፡፡ በወቅቱ በዓለም ላይ የነበረው ሶሻሊዝም እና ካፒታሊዝም የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም የጎራ ልዩነት እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለእንዲህ አይነቱ የልዩነት ፖለቲካ በራቸውን የከፈቱ ኾነው ተገኙ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ጣሊያን አዳፍናቸው የሄደቻቸው የብሔር ልዩነት አደገኛ መርዞች ከዚህም ከዚያም መፈንዳት ጀመሩ፡፡ ልዩነቶቹን በሰከነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ቡድን እየለዩ የሚደረጉ ጥቃቶች የእልክ እና የጥላቻ ፖለቲካን ቦታ ሰጥተውት አለፉ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ክብር ለማስጠበቅ ከሚደረገው የማይታመን ተፈጥሯዊ የሀገር ፍቅር ተጋድሎ በተጻራሪ በየጊዜው የተከሰቱ ፖለቲካዊ ሥብራቶች ያፈሯቸው ቂም እና ቁርሾዎች ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያውያንን ማኀበራዊ ረፍት ሲነሷቸው ይስተዋላል፡፡
እንደ ግለሰብ አብሮ የመኖር ችግር የሌለባቸው ኢትዮጵያውያን እንደ ማኀበረሰብ እና ጎሳ ግን መቋሰል ከጀመሩ ውለው አድረዋል የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡ አሁናዊው የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሳንካዎችም ከእነዚህ ታሪካዊ ስህተቶች እና ስሁት ትርክቶች የመነጩ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡
ጽኑ የሀገረ-መንግሥት ምስረታውን የሚፈታተኑትን ፖለቲካዊ መቋሰሎች በይቅርታ እና በምክክር አክመው መጻዒዋን ኢትዮጵያ ለልጅ ልጆቻቸው የምትመች ለማድረግ ከሽግግር ፍትሕ ጀምሮ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ያሉን የደህንነት ጥናት ተቋም የሥነ-ልቦና አማካሪዋ ወይዘሮ ሰብለ ኃይሌ ናቸው፡፡
የሠላም አማራጮችን ረግጦ እና ውጦ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ አይተነው አላዋጣም የሚሉት አማካሪዋ ለግጭት እና ለጦርነት የሄድነውን ርቀት ያክል ለሠላም መሥራት ይኖርብናል ይላሉ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ኹኔታ በየወቅቱ የተፈጠሩት ፖለቲካዊ ስብራቶች የፈጠሩት መቋሰል የሚስተዋለው፣ በወቅቱ በነበረው ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ድርሻ እና ተሳትፎ ባልነበራቸው ወጣቶች እና የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ነው፡፡
ወይዘሮ ሰብለ ሀገራዊ ምክክሩ ባለፈ ታሪክ እና በትናንት ላይ የሚቋሰሉ ወጣቶችን እና የፖለቲካ ልሂቃኑን በተለየ ሁኔታ ማየት እና ማሳተፍ ይኖርበታል ይላሉ፡፡ ምክክሩ ዘላቂ ሠላም እና ሀገራዊ አንድነትን ማጽናትን ታሳቢ ያደረገ ሂደት ነው የሚሉት አማካሪዋ የትናንት ችግሮች መቋጫ የሚያገኙት በምክክር እና በይቅርታ ብቻ ነው ይላሉ፡፡
በየትኛው የሀገሪቱ ገጠራማ ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ልዩነትን የሚያሰፉ ሃሳቦችን ተሸካሚ ኾነው አይገኙም የሚሉት አማካሪዋ የሀገሪቱን መጻዒ እጣ ፋንታ የሚወስኑት ሰናይ እና ስሁት እሳቤዎች የሚዘወተሩት በከተሞች አካባቢ ባሉ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በመኾኑ ሀገራዊ ምክክሩ ለእነዚህ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል ይላሉ፡፡
ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የቆዩ ሀገራዊ ችግሮች፣ የተዛቡ ትርክቶች እና የተሳሳቱ አረዳዶችን በማረም አዲስ እና ቅቡል የጋራ ሀገራዊ እሳቤዎችን ለማንበር በመኾኑ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች እና የፖለቲካ ልሂቃን በትኩረት ሊያዮት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የምክክሩ ውጤት በትናንት ማንነት እና ምንነት አረዳድ ላይ መቋጫ ማዘጋጀት ብቻ ሳይኾን የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ትሁን? ለሚለው ጥያቄ ስምምነት ላይ መድረስ በመኾኑ ቀና ተሳትፎ እና ትብብርን ይሻል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
