የተከዜ ድልድይ ዳግም ለነዋሪዎች ስጋት መኾኑን የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

104

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሃላ ሰየምት ወረዳን ከዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና ከተማ ሰቆጣ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ ከፈረሰ ሦሥት ዓመታትን አስቆጥሯል።

ከዚህ በፊትም የድልድዩን ግንባታ ክረምት ሳይገባ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል።

ይሁን እንጅ የበልግ ወራትን መግባት ተከትሎ የቁፋሮ ሥራው በጎርፍ በመሞላቱ ስጋት እንደፈጠረባቸው ነው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የገለጹት።

ካነጋገርናቸው መካከል የሰሀላ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ መኮንን በድልድዩ አለመገንባት ምክንያት ወላዶች ፈጥኖ ሕክምና ባለመድረሳቸው ሕይዎት ማለፉን ገልጸዋል፡፡ የወረዳው ነዋሪዎችም በብሔረሰብ አስተዳደሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለማስፈጸምና ለመገልገል እንደተቸገሩም አንስተዋል። አሁን ላይም አካባቢው በጎርፍ በመሞላቱ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ነው የነገሩን።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ውባለም ወልደ ኪሮስ እንዳሉት በድልድዩ አለመገንባት ምክንያት የመንግሥትም ኾነ የግል ጉዳዮችን ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ተጉዞ ለማከናወን አልተቻለም። የተለያዩ አቅርቦቶችን ለማቅረብ ባለመቻሉ ለኑሮ ውድነት መጋለጣቸውን ነው ያነሱት።

ጥያቄውን ለዞን፣ ለክልል የሥራ ኀላፊዎችና ለሕዝብ ተወካዮች ጭምር ማቅረባቸውን አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል፡፡

የዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር መንገድ መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ ሰለሞን እሸቱ፤ ከሰቆጣ ዝቋላ ሰሃላ የሚወስደው የተከዜ ድልድይ የቁፋሮ ሥራው በደለል መሞላቱን በአካል ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። አፋጣኝ መፍትሄ መውስድ ካልተቻለ ወደ ወረዳው ማንኛውንም ቁሳቁስ ለማስገባት እንቅፋት እንደሚኾን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የኮንስትራክሽን ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር ምህረት እውነቴ፤ የዝቋላና ሰሃላ ወረዳዎችን የሚያገናኘው የተከዜ ድልድይ የተከዜ ግድብ መሙላትን ተከትሎ በደለል ጉዳት ሲደርስበት መቆየቱን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ዲዛይን ተሠርቶ ወደ ግንባታ ቢገባም አሁንም ችግር ማጋጠሙን ነው የገለጹት። አሁን ያጋጠመውን ችግርም በዘላቂነት ለመፍታት ዳግም ዲዛይን እንዲሠራ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። ዲዛይኑ እንደተጠናቀቀ ወደ ሥራ ይገባልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ማኅበራዊ ረፍት የነሱ በርካታ ፈተናዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)
Next article“የአንድነትን ዋጋ፣ ክብርና ገጽታን አለመረዳት ልዩነትን ያሰፋል” የፍልስፍና መምህር ጠና ደዎ (ዶ.ር)