“የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ማኅበራዊ ረፍት የነሱ በርካታ ፈተናዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)

61

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ-መንግሥት ታሪክ አያሌ ውጣ ውረዶችን ያስተናገደ እና የተጋፈጠ ሕዝብ ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት ማንነቱንም ሆነ ምንነቱን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አደራጅቶ ሀገር እና ትውልድ ይቀጥል ዘንድ ውድ የሚባሉ መስዋዕትነቶችን ከፍሏል፡፡ ከሌሎች ወንድም እና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ እና በጽናት ቆሞ የጨለማ ዘመን አልፎ የብርሃን ዘመን ይመጣ ዘንድ ተደጋጋሚ የድል ችቦዎችን አቀጣጥሏል፡፡ የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያዊነትም እንደ ዘር ሳይጠፉ ይቆዩ ዘንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የአማራ ሕዝብ ለብዙ ጊዜ ባልተረጋጋ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕይዎት ውስጥ እያለፈ የተረጋጋች ሀገር እንድትፈጠር ምቹ መደላድል ኾኖ የከፉ ፈተናዎችን አሳልፏል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን፣ የተጎነጎኑ ሴራዎችን እና የተሰራጩ ስሁት ትርክቶችን ሁሉ ችሎ ትውልድ የሚመካባት ሀገር እንድትኖር ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ ብዙ ታሪክ ሠርቷል፡፡ በቅርቡ እንኳን በሀገሪቱ ሥር የሰደደውን እና የዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ቅራኔዎች ምክንያት የሆነውን ሥርዓት በለውጥ ለመተካት ፊት ለፊት ተጋፍጦ ውድ ዋጋዎችን ከፍሏል፡፡

ምን ጊዜም ቢሆን ድህረ ለውጥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ መራር የሚባሉ ክስተቶችን አስተናግዶ ያልፋል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ ከሀገረ-መንግሥት ለውጥ ማግስት ጀምሮ በርካታ ሰብዓዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳቶችን ያስከተሉ እኩይ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ በርካቶቹ ጉዳቶች እና ጥቃቶች ያነጣጠሩት ደግሞ ለኢትዮጵያዊነት መጽናት እና መቀጠል እንደምክንያት ሆኖ በሚጠቀሰው የአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ፡፡

የርእሰ መስተዳድሩ አማካሪ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)
በተደጋጋሚ የተፈጠሩት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ቀውሶች ምክንያታቸው የለውጡ ባለቤት የሆነው የአማራ ሕዝብ በለውጡ ተስፋ ቆርጦ እና ተጠራጥሮ እንዲርቅ ለማድረግ ታስቦባቸው የተፈጸሙ ነበሩ ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአማራን ሕዝብ ነባር እሴት እና ሥነ-ልቦናን በወጉ ያልተገነዘቡት የጥፋት ኃይሎች የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች እና የሚጎነጉኗቸው ሴራዎች ዓላማቸው በሕዝቡ እና በትውልዱ ላይ “የተጠቂነት ስሜትን” ለመፍጠር እና ለማሳደግ ያለሙ እንደነበሩ ከተፈጸሙት ድርጊቶቹ መረዳት በቂ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ማኅበራዊ ረፍት የነሱ በርካታ ፈተናዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል ያሉት ዶክተር ደሴ ሕዝቡ ለዘመናት ባነበረው ጥበብ፣ ትዕግስት እና የበዛ ኢትዮጵያዊ ፍቅር የታለፉ ናቸው ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጥቃቶች የሕዝቡ ሆደ ሰፊነት እና የመንግሥት ብስለት ባይታከልባቸው ኖሮ ሀገራዊ ኅልውናን የሚፈታተኑ እና አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ ነው ያሉት፡፡ በግልጽ ከተፈጸመው ጦርነት እና ወረራ ጀምሮ በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ ያሉ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ህቡዕ ጥቃቶች ተፈጽመዋል ይላሉ፡፡

የአማራ ሕዝብ ከለውጡ በፊት እና ማግስት ጀምሮ ያነሳቸው የኅልውና ጥያቄዎች የሕዝቡ፣ የመሪ ድርጅቱ እና የክልሉ መንግሥት ግልጽ ጥያቄዎች በመሆን ነጥረው ወጥተዋል ያሉት አማካሪው፤ የመታገያ ስልቶቹን እና መንገዶቹን በውል መረዳት አለመቻል ለአሁናዊው ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች እንደ ምክንያት ይነሳሉ ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ እንጂ የሌሎችን ወንድም ሕዝቦች መብት የሚጋፉ ጥያቄዎች የሉትም ያሉት ዶክተር ደሴ፤ በርካቶቹ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር መሆኑን አቋም መውሰድ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የሀገሪቷን እና የክልሉን ወቅታዊ እና መሠረታዊ ችግሮች የገመገመ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ለከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩ የመዘጋጀቱ አስፈላጊነትም የጋራ የሆነ ወጥ አቋም፣ አስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት በመፍጠር ለቀጣይ ተልዕኮ መዘጋጀት በማስፈለጉ እንደሆነ ዶክተር ደሴ ያነሳሉ፡፡ ድርጅታዊ ኮንፈረንሶቹ እስከ ታችኛው አመራር ድረስ ወርዶ በፖለቲካ ልሂቃኑ፣ በወጣቶች፣ በሕዝቡ እና በፈጻሚው አካል የጋራ መግባባት ላይ እስኪደረስባቸው ድረስ ይቀጥላሉ ተብሎ ይታሰባል ብለዋል፡፡

ዶክተር ደሴ የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ያልወጣ እና በግልጽ የሚቀነቀኑ ጥያቄዎች ያሉት ሕዝብ በመሆኑ ከሠላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገዶች የራቁ የትግል አቅጣጫዎች ብዙ ርቀት የሚያስጉዙን ስላልሆኑ መንገዶቻችን ማረም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ አደባባይ ላይ ውለው ካደሩ የማንነት፣ የወሰን፣ በየትኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና የመልማት ጥያቄዎች ውጭ ድብቅ ጥያቄ የሌለው ሕዝብ ለሌሎች የሴራ አጀንዳዎች ተጋላጭ የሚሆንበትን መንገድ አመራሩ ኅላፊነት ወስዶ መዝጋት ከዚህ ኮንፈረንስ የሚጠበቅ አንኳር ውጤት መሆን አለበትም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በ90 ቀናት ለመገንባት በእቅድ የተያዙ ትምህርት ቤቶች በበርካታ ቦታዎች ግንባታዎቹ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እየኾኑ ነው” አልማ
Next articleየተከዜ ድልድይ ዳግም ለነዋሪዎች ስጋት መኾኑን የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።