“በ90 ቀናት ለመገንባት በእቅድ የተያዙ ትምህርት ቤቶች በበርካታ ቦታዎች ግንባታዎቹ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እየኾኑ ነው” አልማ

65

ባሕርዳር : ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አልማ በ90 ቀን የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ከ7 ሺህ በላይ መማሪያ ክፍሎችን እያስገነባ መኾኑን አስታውቋል፡፡

ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚተገበረው የአልማ ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ከመጋቢት ወር ጀምሮ 1 ሺህ 832 ብሎኮችን እያስገነባ ነው፡፡

አልማ ሁሉንም የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እስከ መጭው ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ለተጠቃሚዎች ለማስረከብ እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡

በክልሉ ከ80 በመቶ በላይ የሚኾኑት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች እንደኾኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የክልሉ መንግሥት፣ ትምህርት ቢሮ እና አጋሮቹ በክልሉ የሚገኙ እና ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ከ50 በመቶ በታች ዝቅ ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል በኩል ጥረት ከሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች መካከል የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ግንባር ቀደም ድርሻውን ይወስዳል፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ በተለያዩ ሀገራት የተሻለ የአፈጻጸም ውጤት ያመጣ የፕሮጀክት ትግበራ ሥልት ነው ያሉን የአልማ ሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዓለማየሁ ሞገስ ናቸው፡፡ አልማ የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራን በደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ሽዋ ዞኖች በሙከራ ደረጃ ውጤታማነታቸውን አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡ በ2015 ዓ.ም የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም 2 ሺህ 703 የልማት ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ያቀደው አልማ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል 1 ሺህ 832 የመማሪያ ብሎኮችን በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ስልት በ90 ቀናት ለመፈጸም ባለፈው መጋቢት ንቅናቄ ጀምሯል፡፡

አቶ ዓለማየሁ በ90 ቀናት የሚተገበረው የትምህርት ቤቶች ግንባታ ከ7 ሺህ በላይ መማሪያ ክፍሎችን የያዘ እና ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ነው ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ዓለማየሁ በበርካታ ቦታዎች ግንባታዎቹ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እየኾኑ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ሁሉንም የግንባታ ፕሮጀክቶች እስከመጭው ሐምሌ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ለማስረከብ በቅንጅት እየተሠራ እንደኾነም ነግረውናል፡፡

ዳይሬክተሩ በግንባታው የሕዝቡ ተሳትፎ እጅግ አበረታች በመኾኑ የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ለሌሎች ፕሮጀክቶች በአርዓያነት የሚቀርብ ነው ብለዋል፡፡

አልማ ከ95 በመቶ በላይ የልማት ፕሮጀክቶቹ በትምህርት ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleድርጅታዊ ኮንፈረንሱ ውስጣዊ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት መኾኑን ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡
Next article“የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ማኅበራዊ ረፍት የነሱ በርካታ ፈተናዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)