ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ ውስጣዊ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት መኾኑን ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡

94

ባሕርዳር : ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከሀገራዊ ለውጥ ማግስት ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ የልማት፣ የዴሞክራሲ እና የመልካም አሥተዳደር ጅምሮች ታይተዋል፡፡ የሕዝብ መሠረታዊ እና ነባር ጥያቄዎች ተለይተው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ሠላማዊ ትግል ማድረግ ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ነገር ግን በየወቅቱ በሚፈጠሩ አዳዲስ አጀንዳዎች እና መልካቸውን እየቀያየሩ በተፈጠሩ ችግሮች ማኀበራዊ ረፍት ያጣው ሕዝብ ቅሬታዎቹን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ገልጿል፡፡ ይህንን ተከትሎም በክልሉ መንግሥት በመሪ ድርጅቱ እና በመሪዎች መካከል ያሉ ውስንነቶችን ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመለካት ያለመ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ትናንት በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡

ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የአማራ ሕዝብ ነባር እና አዳዲስ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እየተደረገባቸው፤ መግባባት ላይም እየተደረሰባቸው መኾኑን የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በተለይም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ፣ ወቅታዊ እና የሕልውና ጥያቄዎች ግልጽና ተለይተው የሚታወቁ ናቸው ያሉን ከሰሜን ጎንደር ዞን የመጡት የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ወይዘሮ የኛ ነጋ ናቸው፡፡ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች የተለዩ ቢኾኑም ምላሽ በመስጠት በኩል መዘግየት እንደነበር ታይቷል ነው ያሉት፡፡

ፓርቲዉ ለውጡን ተከትሎ የመጣውን ሕዝባዊ ድጋፍ በአግባቡ እንዳይጠቀም በየወቅቱ የሚፈጠሩ አዳዲስ ችግሮች እና ፈተናዎች ረፍት ነስተውት ቆይተዋል ያሉት ወይዘሮ የኛ ችግሮችን ገምግሞ እና ስህተቶችን አርቆ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመለካት ኮንፈረንሱ አስፈላጊ እና ወቅታዊ ነበር ብለዋል፡፡ ሁለተኛ ቀኑን የያዘው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የተያዘለትን ዓላማ በሚያሳካ መልኩ እየተካሄደ ነውም ብለውናል፡፡

የክልሉ ወቅታዊ ችግሮች ከሁለት ዋና ዋና ምንጮች ይቀዳሉ ያሉን የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጋሻው አስማሜ ውስጣዊ እና ውጫዊ ናቸው ይላሉ፡፡ ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ በተለይም በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ክፍተቶች ውስጣዊ ድክመቶች በአግባቡ መፈተሸ አለበት የሚል አቋም ይዟል ነው ያሉት፡፡ በኮንፈረንሱ አመራሩ የመሪነት ሚናውን ለመወጣት የነበሩበትን ጉድለቶች ለይቶ እየተወያየ እና እየተግባባ ነው ብለዋል፡፡

ውስጠ ፓርቲ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የወቅታዊ ችግሮቻችን መውጫ መንገድ ነው ያሉት አቶ ጋሻው ውስጣዊ ችግሮቻችንን በአግባቡ ከፈታን ውጫዊ ፈተናዎችን የሚቋቋም፣ በጥበብ የሚሻገር እና መርህ ላይ ቆሞ የሚታገል በሳል የሐሳብ መሪ መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ሕዝቡም በተሳሳተ ትርክት እና በተሳሳተ አጀንዳ ከሚጠልፉ ኃይሎች በመራቅ የተረጋጋ እና ሰላማዊ ከባቢን መፍጠር ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአምራች ኢንዱስትሪው 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል” የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Next article“በ90 ቀናት ለመገንባት በእቅድ የተያዙ ትምህርት ቤቶች በበርካታ ቦታዎች ግንባታዎቹ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እየኾኑ ነው” አልማ