
ባሕርዳር : ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የ2015 በጀት ዓመት የሶስተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የግብርና፣ የገቢዎችና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች በሰጡት አስተያየት፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የየዘርፎቹ አፈጻጸም ዓመታዊ ዕቅዳቸውን ማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማምረት አቅምን ከ46 በመቶ ወደ 53 በመቶ በማድረስ የዕቅዱን 96 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከውጭ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የምርት አይነቶች ተለይተው በተሠሩ ሥራዎች 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትና የተወሰኑ ምርተችን ደግሞ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ መጀመሪያ ላይ 30 በመቶ ድርሻ የነበረውን የአምራች ዘርፍ የገበያ ድርሻ በዚህ ዓመት 34 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እስካሁን 37 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አንስተዋል።
ቀጣይም የውጭ ምርቶችን ለይቶ በሀገር ውስጥ መርት የመተካት አሠራሮች ላይ በማተኮር ይሠራል ብለዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ በቀጣይ 10 ዓመት በየዓመቱ የስድስት በመቶ ዕድገት ግብ የተያዘለት ግብርናው ዘርፍ በዚህ ዓመት 6 ነጥብ 3 በመቶ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና ላይ ነው ብለዋል።
ከውጭ የሚገኙ ምርቶችን ለመተካት በተሠሩ ሥራዎች ስንዴንና የቢራ ግብስን ሙሉ በሙሉ፣ በሩዝ ደግሞ 50 በመቶ መተካት እንደታቸለ ጠቅሰው በቀጣይ ሶስት ዓመት ሩዝ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ይተካል ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሤ፤ በታክስ ገቢ አሰባስብ በዘጠኝ ወራት የዕቅዱን 98 በመቶ በማሳካት አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መኾኑን ገልጸው የገቢ አፈጻጸም ማደግም ይህን ሀገራዊ የልማት ፍላጎት በአስተማማኝ ደረጃ ለመፈጸም እንደሚያግዝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም ከዕቅድ ማሳካት ባሻገር በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ ግብር ከፋዩን ማኅበረሰብ ግንዛቤና የሕግ ተገዥነት በማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
