
ባሕርዳር : ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
አምባሳደር ምስጋኑ ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶ ዌንፎል ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ኹኔታዎች ላይ ያተኮረ መኾኑን ኢዜአ ዘግቧል።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በጠንካራ ትብብር ትሠራለች ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍልሰት የደቀነውን ችግር ለመቅረፍ ድርጅቱ የሚሠራቸውን ሥራዎች የኢትዮጵያ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋግጠዋል።
ግጭት ባለባቸው የተለያዩ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ለመደገፍ በሚቻልባቸው ኹኔታዎች ላይም ውይይት አድርገዋል።
የዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶ ዌንፎል ድርጅታቸው ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ለውጭ ፍልሰተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዋና ተወካይዋ ኢትዮጵያ የውጭ ፍልሰተኞችን በመቀበል ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተች መኾኗን በመጥቀስ ልዩ ትኩረት የምንሰጣት ሀገር ናት ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት መካከል እያደገ የመጣ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ፤ በቀጣይም ከፍልሰት ጋር በተያያዙ ማዕቀፎች ትብብራቸው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
