
አዲስ አበባ: ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን ተሽከርካሪዎችን ተረክቧል። ድጋፉን ያበረከተው የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ነው።
የተሰጡ አምቡላንሶች ለቅድመ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት የተደራጁ መኾናቸውን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ ጌታቸው ታአ ተናግረዋል ።
በድጋፍ የተሰጡ አምቡላንሶች እና ቀላል ተሽከርካሪዎች ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
አምቡላንሶቹ የማኅበሩ ሕገ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ የሰው ኀይል እና በጀት ተሟልቶላቸው ከዚህ ወር ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
አምቡላንሶች ወደ ሥራ ሲገቡ የማኅበሩን የአምቡላንስ ጣቢያዎች ቁጥርን ያሳድጋል። ማኅበሩ የሚያከናውነውን የሰብዓዊ አገልግሎቶች ለማቀላጠፍ የሚረዱ ናቸውም ተብሏል። ድጋፍ ላደረገው የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበርም ምሥጋና አቅርበዋል።
ማኅበሩ ከተረከበው የአምቡላስ እና ቀላል አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች መካከል አምስት አምቡላስ እና አራት ቀላል ተሽከርካሪዎች ለአማራ ክልል የሚሰጡ መኾናቸው ተጠቅሷል።
ዘጋቢ:- ራሄል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
