
አዲስ አበባ፡ ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በሳይንስ ሙዝየም በፓናል ውይይት ተጀምሯል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያገኘችበትና ተጨባጭ ለውጥ ያመጣችበት የአረንጓዴ ልማት አሻራ ያለፉት 4 ዓመታት 25 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ከታላቁ ህዳሴ ቀጥሎ በራሳችን አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ አደም ፋራህ በመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ ያለፉት 4 ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ አፈፃፀም አመርቂ ነበር በማለት የገለፁ ሲሆን፤ ይህን አፈፃፀም መነሻ በማድረግ ሁለተኛው የአረንጓዴ ልማት አሻራ ለመጀመር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ገልፀዋል።
ያለፈው የአረንጓዴ አሻራ ልማታችን ከባለፈው የተሻሉ ሥራዎች ለመሥራት በሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሠሩ ልማቶችን በመንከባከብ፤ የተተከሉትን ችግኞች አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለውጤታማነት መረባረብ ይገባናል ብለዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ “የአረንጓዴ አሻራ ልማታችን በርካታ የዓለም ሀገራት ያስደመመና ልምዳችንን እንድናካፍል ጥሪ እያደረጉልን ይገኛል” ብለዋል። ይህ ስኬት የሁሉም ሠው ርብርብ ውጤት ነውና ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለማሳካት እንድንዘጋጅ አደራ እላለሁ ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ግብርና ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን በመርሐ-ግብሩ ባለፉት 4 ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም አስታውቋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ዶክተር ግርማ አመንቴ አስታውቀዋል።
በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለው የፓናል ውይይት የፌደራልና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ከፍተኛ ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን በጥናት ላይ የተመሠረተ የአረንጓዴ ልማት የዓለም አቀፍና የኢትዮጵያ ምርጥ ተሞክሮ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 17 ከመቶ መድረሱም በውይይቱ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
