
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በቦሌ ክፍለ ከተማ የአዴፓ ጽሕፈት ቤት እና የአማራ ተወላጆች የአዴፓን 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በጋራ አክብረዋል፡፡
በበዓሉ በነበረ ውይይትም ‹‹ያልተመለሱ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩም ከመደራጀት በመሸሽ አንድነትን ማላላት አይገባም›› ሲሉ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ተናግረዋል፡፡ ተጨባጭነት በሌለው እና በእውነት ላይ ያልቆሙ መረጃዎች የሠላም ፀር በሆኑ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን እየወጡ መሆኑን በማመልከት መቆጣጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ በመደራጀት በኅብረ ብሔራዊነት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየሠራ እንደሆነና ሁሉንም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በማስተባበር የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ መልስ እንዲያገኝ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የቦሌ ክፍለ ከተማ የአዴፓ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መልእክተ ዮሐንስ ተናገረዋል፡፡
የኢሕአዴግ ውሕደት ገለልተኛ የነበሩ ፓርቲዎችን ወደ አንድነት በማምጣት ለብልጽግና እየተጋ በመሆኑ አዴፓ መዋሐድን በመደገፍ ከሕዝቡ ጋር በመደራጀት በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል
የቀድሞው ኢሕዴን የአሁኑ አዴፓ ከምሥረታው ይዞት የመጣውን ኅብረ ብሔራዊነት እሳቤ በኢሕአዴግ ውሕደት መመለሱ የሚደገፍና ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር ዋጋው ከፍ ያለ መሆኑንም አመልክተዋል፤ ለውሕደቱ ሐሳብ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ተጠይቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው -ከአዲስ አበባ