ጎንደር ካለፈው ዓመት የተሻለ ጎብኝ እንዳስተናገደች የከተማዋ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡

192

ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪካዊቷ ከተማ ጎንደር ካለፉት ዓመታት የተሻለ ጎብኝዎችን መሳቧን የከተማዋ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡

የጥንታዊ አብያተ መንግሥታት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ታሪካዊ ሥፍራዎች መዲና ጎንደር የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ትታወቃለች፡፡ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸውን የተዋቡ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን ለማዬት ጎብኚዎች ይመርጧታል፡፡

አስቀድሞ በኮሮና ቫይረስ፣ ከዚያም በነበረው ጦርነት ምክንያት የመናገሻዋ ከተማ ጎንደርን የሚጎበኙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ እንግዶቿ ቁጥር ቀንሰው ነበር፡፡ በጎብኚዎች መቀነስ ምክንያት ጎንደር ማግኘት የሚገባትን ገቢ ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ከጦርነት መቆምና አንጻራዊ ሰላም መፈጠር ወዲህ ግን ጎንደርን የሚጎበኙ ጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን የከተማ አስተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አይቸው አዲሱ ጎንደር ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ቁጥር ያለው ጎብኚ መሳቧን ገልጸዋል፡፡

ወደ ከተማዋ የጥምቀትን በዓል ጨምሮ በሌሎች ጊዜያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን አስተናግዳለች፡፡ ባለፉት አሥር ወራት 50 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ጎንደርን ይጎበኛሉ ተብሎ ታቅዶ ከ69 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ከተማዋ አስተናግዳለች ፡፡ 2 ሺህ 137 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከተማዋን መጎብኘታቸውንም ነው የገለጹት፡፡ ከተማዋ የዕቅዱን 97 በመቶ ማሳከቷንም አስታውቀዋል፡፡

የጎብኚዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በ41 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ደግሞ በአምስት እጥፍ አድጓል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ በጥምቀት በዓል እና በሌሎች ጊዜያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መምጣታቸውን የገለጹት ቡድን መሪው ከጎብኚዎችም 2 ቢሊዮን ብር በከተማዋ ላይ መንቀሳቀሱን ነው የተናገሩት፡፡

በመናገሻዋ ከተማ 70 ሺህ የሚሆኑ እስራኤላውያን ለወራት መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ጎብኚዎች ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩባት የኾነው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመኖሩ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያው ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱንም አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በወረኃ ጥር በርካታ ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ ዝግጅቶችን ማዘጋጀታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የአካባቢው ሰላም እና የከተማዋ ነዋሪዎች የእንግዳ አቀባበል የጎብኚዎችን ቁጥር እንደጨመረውም ነው ያብራሩት፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላማቸውን በሚገባ መጠበቃቸውንም ገልጸዋል፡፡ ቅርሶች የማንነታችን መገጫዎች ናቸው ያሉት ቡድን መሪው የጥንታዊ ቅርሶችን ጉዳት ለማስጠገን ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነግረውናል፡፡ የምሽት ጉብኝት እንዲኖር እና ሌሎች ለቱሪዝም ፍሰቱ አመቺ የኾኑ ሥራዎችን የመሥራት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ጎንደር በቱሪዝም ሰፊ ሃብት ያላት በመኾኗ በሃብቷ ልክ ተጠቃሚ እንድትኾን የማድረግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሸበል በረንታ ወረዳ የዓባይ ሸለቆን ተከትሎ የሚገኘው የማዕድን ሀብት በአግባቡ እየለማ አለመኾኑ ተገለጸ።
Next article“የአረንጓዴ አሻራ በ4 ዓመታት 25 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ከታላቁ ህዳሴ ቀጥሎ በራሳችን አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደምንችል ማሳያ ነው” የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ