በሸበል በረንታ ወረዳ የዓባይ ሸለቆን ተከትሎ የሚገኘው የማዕድን ሀብት በአግባቡ እየለማ አለመኾኑ ተገለጸ።

160

👉የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የወረዳውን የማዕድን ሀብት በ2016 ዓ.ም ለማጥናት አቅጃለሁ ብሏል

ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የዓባይን ሸለቆ ተከትሎ የሚገኘው የማዕድን ሀብት በአግባቡ ተጠንቶ እየለማ አለመኾኑን የወረዳው ማዕድን ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሽመልስ አየለ በወረዳው የዓባይ ወንዝ ሸለቆን ተከትሎ እምቅ የማዕድን ሀብት እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ይህንን ሀብት በውል ለይቶ በማጥናት ወደ ጥቅም የማስገባት ሥራ እስከ አሁን ድረስ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

የወረዳው ማዕድን ልማት ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች በየጊዜው ወደ ሸለቆው እየወረዱ በአካባቢው የሚገኙ ማዕድናትን የመለየት ሥራ እንደሚያከናውኑ አቶ ሽመልስ ተናግረዋል። ይህንን ሀብት በሚገባ አጥንቶ ወደ ጥቅም ለማስገባት ግን በክልል ደረጃ የተቀናጀ የከፍተኛ ባለሙያዎች ጥናት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት። የክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ባለሙያዎች ተመድበው እንደሚመጡ ቃል በመገባቱ በመጠባበቅ ላይ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል።

ሸበል በረንታ ወረዳ በዓባይ ወንዝ የተከበበ በመኾኑ የውኃ ችግር የሌለበት እና ለማንኛውም የማዕድን ኢንቨስትመንት የተመቸ ነው። አካባቢው ሰላማዊ እና የሥራ ወዳድ ማኅበረሰብ መኖሪያ ስለመኾኑም አቶ ሽመልስ ተናግረዋል። ባለሀብቶች ወደ አካባቢው በመምጣት በዘርፉ ቢሰማሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያገኙ እና ትርፋማ እንደሚኾኑም መልእክት አስተላልፈዋል።

አሁን ላይ ግዙፍ የኾነው በረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ በወረዳው እየተገነባ ስለመኮኑም አቶ ሽመልስ ገልጸዋል። የአካባቢውን እምቅ የማዕድን ሀብት ለመጠቀም ሌሎች ትላልቅ ፋብሪካዎች እንደሚያስፈልጉም አመላክተዋል።
በሸበል በረንታ ወረዳ ማዕድን ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የማዕድን ባለሙያው አቶ ጌታቸው አድማሱ በወረዳው በርካታ ዓይነት የማዕድን ክምችት እንደሚገኝ ገልጸዋል። ለዓብነትም እንደ ብረት፣ኒኬል፣ ኮፐር፣ ወርቅ፣ እብነበረድ፣ ድንጋይ ከሰል፣ ጅብሰም፣ ላይም ስቶን እና የተለያዩ ጌጣጌጦችን ለመሥራት የሚያገለግሉ በርካታ ማዕድናት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በወረዳው 15ቱ ቀበሌዎች ውስጥ ማዕድናት ስለመኖራቸው የገለጹት ባለሙያው በተለይም ወረጎ በተባለው ቀበሌ ላይ እምቅ የማዕድን ሀብት ስለመኖሩ ገልጸዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን የማዕድን ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ መልሰው ምሥራቅ ጎጃም ዞን በርካታ የማዕድን ፀጋዎች ያሉት ነው ብለዋል። ለመኪና፣ ሞባይል እና ላፕቶፕ ባትሪ መሥሪያነት የሚያገለግል ሊትየም የተባለ ማዕድን በስፋት እንደሚገኝ ጠቁመዋል። እንደ ግራናይት እና ሲሊካ ሳንድ የመሳሰሉ የግንባታ ግብዓት ለማምረት የሚያገለግሉ ማዕድናትም በዞኑ ይገኛሉ። በእነብሴ፣ ሸበል እና ደብረ ኤልያስ አካባቢ ደግሞ የኦፓል ምርት እንደሚገኝ ተለይቷል ብለዋል።
ዞኑ “ማዕድን አዲስ የንጋት ተስፋ ለዞናችን” የሚል መሪ መልእክት በመያዝ የማዕድን ጸጋዎችን ወደ ሀብትነት በመቀየር ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ወይዘሮ የሻረግ ተናግረዋል።

በተለይም በሸበል በረንታ ወረዳ የዓባይን ሸለቆ ተከትሎ በርካታ የማዕድን ሃብት ስለመኖሩ አመላካች ጥናት መደረጉን ገልጸዋል። ይህንን እድል ወደ ሃብትነት ለመቀየር ግን የክልሉ ማዕድን ሀብት ቢሮም ተገቢውን ጥናት እንዳላደረገ ነው መምሪያ ኀላፊዋ የገለጹት።

የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታምራት ደምሴ በ2016 ዓ.ም በሸበል በረንታ ወረዳ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን ዓይነት እና የክምችት መጠን በጥልቅ ለማጥናት እቅድ ተይዟል ብለዋል። ጥናቱ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የሚሠራ ይሆናል። እንደ አቶ ታምራት ገለጻ የማዕድናቱ ጥናት ከተካሄደ በኋላ በዘርፉ የሚሠማራ ባለሀብት በማፈላለግ ወደሥራ ይገባል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ክልል የመሪዎች ኮንፈረንስ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየመከረ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
Next articleጎንደር ካለፈው ዓመት የተሻለ ጎብኝ እንዳስተናገደች የከተማዋ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡