“የአማራ ክልል የመሪዎች ኮንፈረንስ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየመከረ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

512

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከፍተኛ እና የመካከለኛ መሪዎች ኮንፈረስ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡ የኮንፈረንሱን ውሎ አስመልክተው የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸው ኮንፈረንሱ ልዩ የኾነና በአንኳር ጉዳዮች ተወያይቶ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ መኾኑንም ገልጸዋል። ኮንፈረንሱ ግቡን እና ዓላማውን በሚያሳካ መልኩ እየተካሄደ መኾኑንም ተናግረዋል።

ኮንፈረንሱ በውሎው ውይይት ክልላዊ ኹኔታውን የሚያነሳና የሚተነትን፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታው አልጋ በአልጋ እንዳልመጣ የሚያስታውስ፣ የተገኙ ድሎች ሁሉ ያለፈተና እንዳልተገኙ የዳሰሰ ነው ብለዋል፡፡ በፈተናዎች ባለመንበርከክ፣ በፈተናዎች እየፀኑ፣ ፈተናዎችን ወደ እድልና ድል እየቀየሩ ለተሻለ ድል መዘጋጀት እንደሚገባ መነሳቱንም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን የሀገረ መንግሥት ግንባታና አሁን ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደመነሻ በመውሰድ መምከሩንም ገልጸዋል፡፡ በተለይም በለውጡ ሂደት ለለውጡ መነሻ ምክንያቶች ምን ነበሩ፣ የለውጡ ሂደትስ ምን ይመስላል የሚለው ላይ መምከሩንም አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ዋና እና መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየመከረ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ይፈልጋል ያሉት ኃላፊው ሕዝቡ በሚፈልገው መልኩ መምራት እንዲቻል የሚያስችል አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነውም ብለዋል፡፡

የክልሉ አሁናዊ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ምን አይነት መልካም ነገሮች አሉ? ፈተናዎችን እንዴት አድርገን ወደ ድል እንቀይራለን የሚለው በስፋት እየተነሳ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ጠላትን እያበዙ ወዳጅን እየቀነሱ የሚሄዱ፣ መሪን ከሕዝብ፣ ሕዝብን ከመሪ የሚነጥሉ አካሄዶች መስተካከል እንደሚገባቸውም በስፋት እየተነሱ ውይይት እየተካሄባቸው ነውም ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ልዕልና ላይ መሠረት ያደረገ ትግል አስፈላጊ እንደሆነ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

ውስጣዊ ችግሮቻችን ላይ አተኩረን የክልሉን አንድነት በመፍጠር ነው የአማራ ክልል መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉትም ብለዋል፡፡ የሕዝብ አንድነትና የመሪዎች አንድነት ሲጠናከር የሕዝብ ጥያቄዎች እንደሚፈቱም አመላክተዋል፡፡
አንኳር የኾኑ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ መኾኑን የሚያስገነዘብ ኮንፈረንስ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ኮንፈረሱ ነጻ ውይይት እየተደረገበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ መሪዎች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን ተገንዝበው ለወቅቱ የሚመጥን ጽናት፣ ቁርጠኝነት እና ለመስዋዕትነት ዝግጁ መሆን እንደሚያሻ በኮንፈረሱ ውይይት እየተደረገበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ተደራራቢ ችግር እየተከሰተ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው በቁጭት በመነሳት ችግሮችን መፍታት በሚቻልባቸው እና የአማራን ሕዝብ ክብር የሚመጥን ሥራ መሥራት በሚቻልበት ጉዳይም መምከሩን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ተረጋግቶ ዋነኛ ጥያቄዎች ላይ አተኩሮ እንዲሠራ የፖለቲካ ሥነ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ክልሉ ይዟቸው የሚወጡ አቋሞች ወደ ታች ወርደው ውይይት እንደሚደረግባቸውም አስታውቀዋል፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚኖረን ግንኙነት በምን ላይ መመስረት አለበት የሚለው ጉዳይም ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ክልሉ ላይ ሰላም ሊያሰፍን የሚችል ቁርጠኝነትና አንድነት እንዲኖር ይፈለጋልም ነው ያሉት፡፡ ጽናትን ተላብሶ የሕዝብ አገልጋይ መኾን ከኮንፈረንሱ በኋላ የሚጠበቅ ግብ ነው ብለዋል፡፡ ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል መሪዎች ለሕዝቡ ምን አይነት ትግል እያደረጉ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያለመረዳት ችግሮች መኖራቸውንም ያነሱት ኃላፊው ኮንፈረንሱ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም አንስተዋል፡፡

በቀሪ ቀናት በሚኖሩ ውይይቶች አንኳር አንኳር ጉዳዮች እየተነሱ ይመከርባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የኮንፈረንሱ ውሎዎች በተከታታይ ለሕዝቡ እንደሚያደርሱና ሕዝቡም ትክክለኛ መረጃዎችን በመከታተል በትዕግስት እንዲጠባበቅ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከ‘ገርልስ ኢፌክት’ የኢትዮጵያ ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያዩ
Next articleበሸበል በረንታ ወረዳ የዓባይ ሸለቆን ተከትሎ የሚገኘው የማዕድን ሀብት በአግባቡ እየለማ አለመኾኑ ተገለጸ።