
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የማኅበረሰብ አገልግሎቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም ለሀገር ራስ ምታት የኾነዉን የዉጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ረገድ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስገኘቱ ተነግሯል፡፡ በሀገር ዉስጥ ተኪ ምርቶችን በማቅረብ ለእነዚህ ምርቶች ሊወጣ የነበረዉን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የዉጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል፡፡
በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣዉን የኢንቨስትመንት ደኅንነት ለመጠበቅ የመንግሥት መዋቅሩ ከሚያደርገዉ ጥበቃ ጎን ለጎን ፓርኩ በዘርፉ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑም ነው የተገለጸው፡፡ የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ደኅንነት አገልግሎት ኀላፊ ኮማንደር ፍቅሩ ሳኅሌ እንዳሉት የእሳትና ድንገተኛ ብርጌድ በማቋቋም የፓርኩንም የከተማዋንም ደኅንነት ለመጠበቅ በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ የድንገተኛ እና የእሳት አደጋዎችን ለመቆጣጠር በተደረገዉ ጥረትም የፓርኩ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ቡድን የተጫወተዉ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል፡፡ በከተማዋ ያጋጠሙ 7 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ በፍጥነት በመቆጣጠር ረገድም የፓርኩ ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ነው ኮማንደር ፍቅሩ የገለጹት።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ በዚህና መሰል ተግባራት ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የፓርኩ ሥራ አሥኪያጅ የሽጥላ ሙሉጌታ ናቸው። የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑም አመላክተዋል።
ከ3 ሺህ 300 በላይ ሠራተኞች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተጠቃሚ ሲኾኑ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን በማድረግም አይነተኛ ሚናውን እየተጫወተ ነው ብለዋል።ፓርኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የተከበረዉን የእሳትና አደጋ ሠራተኞች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ አክብሯል።
‘ጀግኖቻችንን እናክብር’ በሚል መሪ ሃሳብ በተከበረው በዚህ እለት የፓርኩ ሠራተኞች፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የአምራች ኢንዱስትሪው ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!