በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት እንዲጠናከር ተጠየቀ።

70

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት እንዲጠናከር ተጠይቋል። ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቱን ሊያጠናክር የሚችል ፖሊሲ ጭምር ሊኖር እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ አላቸው። በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመኾኑ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በመፍታት ሰላም እንዲፈጠር ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ በሕቡዕ ተፈጽመው በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮችን ጭምር በባሕላዊ መንገዶች በመለየት አጥፊውን የመቅጣት እና ተበዳዩን የመካስ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልኾነባቸው የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን በማስፈን የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

በዚህም ከመደበኛ የፍትሕ ሥርዓቱ በተሻለ መንገድ ችግር ፈች እና በማኅበረሰቡም ተመራጭ መኾናቸውን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር ሞገስ ሚካኤል (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ከአሚኮ ጋር ባደረገው ቆይታ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች በሕዝቡ ነባር የግብረገብ መሰረቶች ላይ መነሻ ያደረገ በመኾኑ ተዓማኒነት አላቸው፡፡ የሽማግሌ መረጣ፣ የድርድር ጊዜና ቦታ ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጪ በኾነ መንገድ በበዳይ እና በተበዳይ ቡድኖች በኩል ስለሚወሰን በሽማግሌዎቹ የተላለፈው ውሳኔ በኹለቱም በኩል ተቀባይነት እንዳላቸውም መምሕሩ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሐመድ ይማም እንዳሉት ደግሞ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች የመንግሥት ሥርዓት ጠንካራ ባልነበረበት ወቅት የማኅበረሰቡን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ከመደበኛ የፍትሕ ተቋማት የበለጠ ተመራጭና ጠቀሜታቸውም የጎላ ነው፡፡ የሽምግልና ሥርዓቱ በማኅበረሰቡ ለምን ተመራጭ ኾኑ? ለሚለው ጥያቄ ምሁራኑ ያብራራሉ፡፡

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች፡-

👉 በማኅበረሰቡ የቆዩ እምነቶች እና ሥርዓቶች ላይ የተመሰረቱ በመኾናቸው የሽማግሌዎችን ውሳኔዎች ለመፈጸም አስገዳጅነት የላቸውም፡፡

👉ሥርዓቱ ግልሰቦች ቤት፣ በሃይማኖታዊ ተቋማት እና የበዓላትን ቀን መሰረት በማድረግ ስለሚካሔዱ በመደበኛ የፍትሕ ተቋማት ፍትሕ ለማግኘት የሚወጣውን የትራንስፖርት እና መሰል ወጪን ያስቀራሉ፤ የሥራ ሰዓት እና ጉልበት እንዳይባክንም ያደርጋሉ፡፡

👉 ሽማግሌዎችን እና የሽምግልና ጊዜ እና ቦታን በመቀየር የሃይማኖት ተቋማት ጣልቃ እንዲገቡ ስለሚያደርጉ ባሕላዊ ሽምግልናው የተሻለ ተቀባይነት አለው፡፡

👉 በሃይማኖት ተቋማት መከናወናቸው ደግሞ ግጭት ውስጥ በገቡ አካላት፣ በምስክሮች እና በሽማግሌዎች ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ የሥነ ልቦና ጫና ስለሚፈጥሩ ምስክሮች ለመመስከር፣ ሽማግሌዎች ውሳኔ ለመስጠት፣ ግጭት ውስጥ የገቡት አካላት ደግሞ የተላለፈውን ውሳኔ ለመቀበል እድል የሚፈጥር ነው፡፡

👉 የሽምግልናው የመጨረሻ ግብ ፍቅርና ዘላቂ ሰላምን በሚያሰፍን መንገድ ማስታረቅ ላይ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

👉 ግጭት ፈጣሪዎቹ ከበቀል እና ከቂም በመላቀቅ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡

መደበኛ የፍትሕ ተቋማት፡-

👉 በአብዛኛው በገንዘብ፣ በጉልበት እና በጊዜ አባካኝ ከመኾናቸው ባሻገር አገልግሎታቸው በሥራ ቀናት መኾኑ ተመራጭነታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

👉 ዓላማውም አጥፊውን መለየት እና መቅጣት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

👉 ዋና ዓላማው ደግሞ ማስታረቅ ላይ የተመሰረተ ሳይኾን አጥፊውን በገንዘብ፣ በእስራት እንዲቀጣ ማድርግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትውልድ መካከል ቂም በቀል የሚያነግስ ነው፡፡ በግድያ ምክንያት በእስራት ተቀጥቶ ውሳኔውን ጨርሶ የወጣ ግለሰብ ጉዳዩ በሽምግልና ካላለቀ አንዳንድ ጊዜ ችግሮች እንደገና ሊያገረሽ ይችላል።

👉 ውሳኔዎች በፖሊስ እና በፍርድ ቤት በመሳሰሉ አስገዳጅ ኀይሎች ሥለሚፈጸም ባሕላዊውን ሥርዓት የተሻለ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓትን ከዘመኑ ጋር ለማስቀጠል መጠነኛም ቢኾን ደንብ የማዘጋጀትና የቅጣት አይነቶችን ወጥ የማድረግ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ይሁን እንጅ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በሥራቸው ላይ እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ የነበራቸውን እሴት፣ ወግና ልማድ እንዲያስቀጥሉ ከማገዝ ይልቅ ከዓላማቸው ውጭ እንዲሠሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

መምህሩ ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ሚናቸው የጎላ በመኾኑ አኹን በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጥ የኾነ ተቋማዊ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የሥልጠና፣ የቁሳቁስ እና የበጀት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የሽምግልና ሥርዓቱን ሊያጠናክር የሚችል አዋጅ እና ፖሊሲ ጭምር ማዘጋጀት እንደሚገባ ነው መምህሩ የመከሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያደሩ ችግሮቻችን ለቆርቋሪዎችም ለተቆርቋሪዎችም የሴራ ፖለቲካ ትንታኔ መነሻዎች ኾነዋል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleበሐሳብ ልዩነት መካከል የተጋመደ ሕዝባዊ አንድነትን መፍጠር የአማራ ሕዝብ ነባር እሴት መኾኑን ማሳየት ይገባል ተባለ፡፡