
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡ ኮንፈረንሱ በአማራ ክልል ወቅታዊ ኹኔታዎች እና የቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እና ለማረም የችግሮቹን መንስኤ እና መፍትሔ በውል መረዳት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ በተለይም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠሩ የተሳሳቱ ትርክቶች ምክንያት ውስብስብ ፈተናዎችን አልፏል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሮቹን የፈታባቸው እና ፈተናዎቹን የተሻገረባቸው ጥበብ የክልሉን ሕዝብ የሥነ-ልቦና ልዕልና ያመላክታል ብለዋል፡፡ በተደጋጋሚ እና ኾን ተብለው በሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎች እና ትርክቶች ምክንያት በክልሉ የተጠቂነት ስሜት እንዲጎለብት የሚሠሩ ኀይሎች ቢኖሩም ይህ የአማራን ሕዝብ ትክክለኛ ማንነት ካለማወቅ የሚመነጭ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የተንከባለሉ የሕዝብ ችግሮች አሉ፡፡ ማንነት እና ወሰን፣ የተዛባ ትርክት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የዜጎች በፈለጉት አካባቢ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሰብዓዊ መብቶች እና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች አሉ ያሉት ዶክተር ይልቃል “ያደሩ ችግሮቻችን ለቆርቋሪዎችም ለተቆርቋሪዎችም የሴራ ፖለቲካ ትንታኔ መነሻዎች ኾነዋል” ነው ያሉት፡፡ የጠራ አቋም፣ ትክክለኛ የትግል መሥመር እና በኢትዮጵያዊ ጥላ ሥር ተሰባስቦ መመለስ ግድ ነው ብለዋል፡፡
የቀደሙ የሕዝብ ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ አለመመለሳቸው በየጊዜው ከሚፈጠሩ ቅሬታዎች ጋር ተደራርበው ሕዝብ በመረጠው ፓርቲ ላይ እምነት እንዲያጣ የሚሠሩ ኅይሎች በግልጽ እና በህቡዕ እንዳሉ ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በሚገባ ታግሎ እና ነጥሮ መውጣት የአማራሩን የተግባር፣ የአስተሳሰብ እና የጽናት አንድነትን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የክልሉን ሠላም ማናጋት፣ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴውን መግታት እና ማኅበራዊ እረፍት መንሳትን የትግል ሥልት ያደረጉ ኀይሎችም ለክልሉ ሕዝብ እረፍትን የማይሹ ናቸው ብለዋል፡፡ በቅርቡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ አድማዎች ቢሳኩ ኖሮ በየትኛውም መንገድ የክልሉን ሕዝብ አይጠቅሙም ያሉት ዶክተር ይልቃል ባለቤቶቻቸው በግልጽ የማይታወቁ እና የተሳሳቱ ሕገ ወጥ ሂደቶችን ሕዝብ እንዲታገላቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ችግሮቻችን ብቻ ሳይኾኑ አቅሞቻችንም ከውጭ ሳይኾኑ ከውስጣዊ አንድነቶቻችን የሚመነጩ ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በዚህ ኮንፈረንስ የክልሉን አመራር ውስጣዊ አንድነት የሚያጸና ውይይት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል ማድረግ፣ ወደ አንድ አስተሳሰብ መምጣት፣ የጠራ መስመር መያዝ እና በጽናት መታገል ከዚህ ኮንፈረንስ የሚጠበቅ ውጤት ነውም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!