
ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የከፍተኛ እና መካከለኛ አመራር ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይዘልቃል የተባለው የፓርቲው ከፍተኛ መሪዎች ኮንፈረንስ “ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ሃሳብ ተጀምሯል፡፡
ለዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሠላም ሥምምነት ከተቋጨ ገና አንድ ዓመት እንኳን አልተቆጠረም ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የሠላም ሥምምነት እንፈራረም እንጂ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እና ለማጽናት ብዙ መሥራትን ይጠይቀናል ብለዋል፡፡
በክልሉ ጦርነቱ ያደረሰው ምስቅልቅል ብዙ እና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉት በመኾኑ አሁንም ወገኖቻችንን በዘላቂነት ለማቋቋም እና ጦርነቱ ያደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ለመቋቋም ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል ዶክተር ይልቃል፡፡
ነገር ግን አሉ ርእሰ መሥተዳድሩ ያደሩ ችግሮችን እያከኩ፣ ወቅታዊ የሕዝብ ችግሮችን እየታከኩ እና በሬ ወለደ የሐሰት መረጃ እያሰራጩ ያሉ አካላት የሚፈጥሯቸው አዳዲስ አጀንዳዎች የክልሉ መንግሥት ብዙ እንዳይሠራ እንቅፋት ኾነዋል፡፡
ወገኖቻችንን ሳናቋቁም እና ከጦርነቱ ጉዳት በሚገባ ሳናገግም በወቅታዊ አጀንዳዎች እና በውስጣዊ ችግሮቻችን በብዙው ተፈትነናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የገጠሙን ፈተናዎች በጽናት እና በብስለት ለመሻገር የውስጥ አንድነትን ማጎልበት ወቅቱ የሚጠይቀው ቀዳሚ ሥራ ነው ብለዋል፡፡ አሁን የሚካሄደው የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ኮንፈረንስም ይህንን ውስጣዊ አንድነት እና የፖለቲካ ከፍታ ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ያደሩ፣ በግልጽ የሚታወቁ እና የሌሎችን ህልውናም ኾነ መብት የማይጋፉ ሰዋዊ ጥያቄዎች ናቸው ያሉት ዶክተር ይልቃል ወጥ አቋም፣ የተስተካከለ የትግል ስልት እና የተሰባሰበ ኅብረት ያለው ባለመኾኑ ብዙም ርቀት አልተሄደባቸውም ነበር ብለዋል፡፡ የክልሉ መሪዎች ችግሮችን እየገመገሙ፣ ህጸጾችን እያረሙ እና የተሻለ በመፈጸም ሕዝብ እና ታሪክ የጣሉበትን ኅላፊነት መወጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ በንግግራቸው የአማራ ሕዝብ በሕግ ያለፈ፣ በሕግ የኖረ እና በሕግ የሚያምን ቀደምት ሥርዓት ያነበረ ሕዝብ ነው፡፡ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ አካሄዶችን በፍጥነት ማረም ይገባልም ብለዋል፡፡
የተለየ፣ ያልተናበበ፣ በህቡዕ የተደራጀ እና የተሳሳተ የትግል ሥልት መከተል ውጤቱ ምን እንደነበር ከዘውዳዊ ሥርዓት ማክተም ጀምሮ በነበሩ የሽግግር ወቅቶች አይተናል ያሉት ዶክተር ይልቃል “የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር በመኾኑ ወጥ አቋም ይዞ መታገል ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!