“የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል አምራች እና ሸማች የሚገናኙበት 34 የገበያ ማዕከላት ለይተናል” የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ

118

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች በመኖራቸው የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በባሕርዳር ከተማ ባደረገው የገበያ ቅኝት ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ዋጋ መጨመር እንዳሳየ ተመልክቷል፡፡

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያል ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አበጀ አየሁ የኑሮ ውድነቱን ባለበት ለማስቆም ቢሮው የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ቢሮው እስከ ታች ያለውን መዋቅር በመጠቀም መድረኮችን አዘጋጅቶ ለፈጻሚዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሠርቷል፤ ተዘዋዋሪ ብድር በመመደብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚያቀርቡበት መንገድ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

ባለፉት 10 ወራት ከ289 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 231 ሺህ 315 ኩንታል ጤፍ፣ 221ሺህ 315 ኩንታል የጥራጥሬ ምርቶች፣ 38 ሺህ 137 ኪሎ ግራም ፓስታ እና ማካሮኒ፣ 2 ሚሊዮን 529 ሺህ 97 ሊትር ዘይት ኑሮአቸውን በዝቅተኛ ገቢ ለሚመሩ ሸማቾች በዩኔኖች፣ በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና በሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ተደራሽ ማድረጉን እና የማኅበረሰቡን ችግር መቅረፍ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልምት ቢሮ ባለሙያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በስድስት ዙር በማሰማራት ያለአግባብ የሸቀጦችን ዋጋ በማናር ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የማድረግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ ያለንግድ ፈቃድ የሚሠሩ ነጋዴዎች እና ከካፒታል በላይ ሲነግዱ በቆዩ፣ ሸቀጦችን ከዝነው በተገኙ ነጋዴዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡ በተለይ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶችን የማስወገድ፣ የተከማቹ ምርቶችን ለተጠቃሚው የማስተላለፍ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ወረዳዎች፣ ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የነዋሪዎችን ችግር ለመቅረፍ ተጨማሪ ተዘዋዋሪ ብድር እንዲያመቻቹ የማድረጉ ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

አቶ አበጀ ቢሮው የእሁድ እና የቅዳሜ ገበያ በማቋቋም ሸማቾች ቀጥታ ከሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ከዩኔኖች እና ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚገናኙበት መንገድ መመቻቸቱንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም እስካሁን 34 የገበያ ማዕከላት ተለይተዋል፡፡ 31 ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 15 የገበያ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሚፈልገውን ምርት በሚፈልገው ቀን ማግኘት የማይችል ማንኛውም ሸማች ከገበያ ማዕከላት ማግኘት እንደሚችልም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ጎን ለጎን በተዘዋዋሪ ብድር ምርት የማቅረቡ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኀላፊው የዋጋ ጭማሪን ለማስቆም የንግድ እና የገበያ ልማት ቢሮ ሠራተኞች በቂ ባለመኾናቸው ማኅበረሰቡ ሕገወጦችን በማጋለጥ፣ ነጋዴዎችን የዋጋ ዝርዝር እንዲለጥፉ በመጠየቅ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ኅብረተሰቡም በተጠየቀው ዋጋ ከመግዛት ይልቅ ዙሪያ መለሥ ቅኝት በማድረግ ሁኔታዎችን ማጥናት፤ ጉዳዩ ከምን ጋር እንደሚያያዝ መረዳት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የተለየ ነገር ሲመለከቱም ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ሕገወጦች ከገቡበት ሕገወጥ ተግባር የሚወጡበትን መንገድ ማመላከት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ሸማቾች ከሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኔኖች እና አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሸመት ልምዳቸውን ማዳበር፣ ማኅበራቱን ማጠናከር፤ እና መደገፍ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

በየተዋረዱ የሚገኙ ባለሙያዎች ማኅበረሰቡን የሚበዘብዙ ስግብግብ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማኅበረሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አባት ያሳመራት፣ ትውልድ የሚኮራባት”
Next article“የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም ይሰጣል” ትምህርት ሚኒስቴር