
ባሕርዳር : ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምድር ያልታሰበውን አደረጉት፣ የዓለምን ጥበብ ናቁት፣ ከእርሳቸው በፊት ያልነበረውን ጥበብ ለዓለሙ ሁሉ አሳዩት፣ ጨርሰው ጀመሩ፣ የምድራዊት እና የሰማያዊት ኢየሩሳሌምን አምሳል በዓለት ላይ ሠሩ፣ በቅዱስ መጽሐፍ ያለውን ምስጢር በዓለት ላይ አኖሩ፡፡
የእጅ ሥራቸው እያደረ አዲስ ነገር የሚታይበት፣ አዲስ ሚስጥር የሚፈታበት፣ አዲስ ጥበብ የሚፈልቅበት፣ ያልተመረመረ እጅግ የከበረ ምስጢር የመላበት ነው፡፡ ያለ ምክንያት የሠሩት፣ ያለ ምልክት የቀረጹት አንድም ነገር የለም፡፡ ሁሉም ምስጢር ይመሰጠርበታል፣ ሃይማኖት ይነገርበታል፣ ታሪክ ይዘከርበታል፣ ኀያልነት እና ረቂቅ ጥበብ ይገለጥበታል እንጂ፡፡
ራሳቸው የሚኖሩበት፣ በዙፋን ተቀምጠው የሚንደላቀቁበት፣ ወይን የሚያስቀዱበት፣ ጮማ የሚያስቆርጡበት፣ ከሰገነት ወደ ሰገነት የሚረማመዱበት፣ በተመቸ መኝታ የሚያርፉበት፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ የሚመላለሱበት፣ በዙሪያ ገባው የከበረ አጥር የታጠረበት፣ በአጥሩ ዙሪያም እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ ጦረኞች የሚቆሙበት ቤተ መንግሥት አልሠሩም፡፡ ከዚያ ይልቅስ የአምላካቸው ስም የሚመሰገንበት፣ በሰርክ ክብሩ የሚገለጥበት፣ ስጋና ደሙ የሚፈተትበት፣ ቅዱሳኑ ለምሥጋና ቆመው ውለው ለምሥጋና የሚያድሩበት፣ ሕዝብ ሁሉ የአምላክን ድንቅ ሥራ ለመመስከርና ለማመስገን ከየአቅጣጫው የሚሰባሰብበት፣ ሃይማኖት የሚጸናበት፣ በረከትና ረድዔት የሚወርድበት፣ ሰላምና ፍቅር የሚሰበክበት፣ የአምላክ መንፈስ ረብቦ የሚኖርበት፣ ሊቃውንት እንደ ገነት ምንጭ የሚፈልቁበት ድንቅ ቤተ መቅደስ አነጹ እንጂ፡፡
ዘመናቸውን አላባከኗትም፣ ነብሳቸውን ለአምላካቸው፣ ስጋቸውን ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው አስገዝተው ኖሩ እንጂ፡፡ ቅዱስ ወ ንጉሥ ላሊበላ፡፡ ሀገራቸው ኢትዮጵያን አብዝተው ይወዷታል፣ ለክብሯም አብዝተው ይጨነቁላታል፤ ቅዱስ ናቸውና ለሰማዩ መንግሥት ነብሳቸውን አዘጋጇት፣ ንጉሥ ናቸውና ሀገራቸውን በጥበብ እና በሞገስ አገለገሏት፣ ዓለም ሁሉ እንዲያያት፣ ኀያልነቷን እና ቀዳሚነቷን እያደነቀ ስሟን እንዲጠራት፣ እየፈለገ እንዲመጣባት፣ በመጣም ጊዜ ደስ እንዲሰኝባት፣ ታሪክና ሃይማኖት እንዲማርባት ታላቅ ነገርን ቀርጸው አስቀመጡላት፡፡
እርሳቸው የሠሩትን አይነት የሠራ ከዬት ይገኛል? የጥበባቸውን ልክ እጹብ እያሉ ያደንቁታል እንጂ ሌላ ምን ይሉታል?
ኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት ነግሠውባታል፣ በተዋበው ዙፋን ላይ ተቀምጠው፣ የከበረውን ዘውድና አክሊል ደፍተው፣ ያጌጠውን በትረ መንግሥት ጨብጠው፣ አምላካቸውን በመፍራት፣ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው በመሳሳት በጥበብ እና በሞገስ አገልግለዋታል፣ ለክብሯ ተዋድቀውላታል፣ ለስሟ ታላቅ ነገርን ሠርተውላታል፣ ለሠንደቋ ደም አፍስሰውላታል፣ አጥንት ከስክሰውላታል፣ ሕይወት ገብረውላታል፡፡
የታላላቆቹ ነገሥታት አሻራዎች፣ የጥበብ ውጤቶች ዛሬም ኢትዮጵያን በዓለሙ ፊት ሁሉ ከፍ ከፍ ያደርጓታል፣ ድንቅና ብርቅ ያሰኟታል፣ በምድሯ በአምላክ እጅ የተፈጠሩትን፣ በጠቢባን እጆች የተሠሩትን፣ ሳይበረዙና ሳይሰረዙ ዘመናትን የተሻገሩትን ለማዬት ብዙዎች ወደ ምድሯ ይመጣሉ፣ በመጡም ጊዜ ደስ ይሰኛሉ፣ የኢትዮጵያ ቀደምትነት፣ የኢትዮጵያውያንንም ጠቢብነት ያውቃሉ፡፡
ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ የሠሯቸው ድንቅ አብያተ ክርስቲያናት ሰርክ አዲስ እየኾኑ የዓለምን ቀልብ ይስባሉ፣ ብዙዎች የእርሳቸውን ድንቅ ሥራዎች ለማዬት ወደ ኢትዮጵያ ይመለከታሉ፣ ወደ ኢትዮጵያም ይጓዛሉ፣ ስለ ኢትዮጵያም ይሰማሉ፣ ስለ ኢትዮጵያም ያነብባሉ፡፡ ኢትዮጵያውያንም ታሪካቸውን፣ ሃይማኖታቸውን እና የአባቶቻቸውን ጥበብ ለማዬት ወደዚያች ሥፍራ በየጊዜው ይገሰግሳሉ፡፡ አባት አሳምረው የሠሯት፣ ትውልድ የሚኮራባት ያቺ ውብ ሥፍራ የብዙዎች መገናኛ ናት፡፡
በቅዱስ ወ ንጉሥ ላሊበላ የተሰየመችውና እጅግ የረቀቁ ምስጢራትን አቅፋ የያዘችው ላሊበላ ከተማ ታሪክ የሚነገርባት፣ ሃይማኖት የሚሰበክባት፣ ምስጢር የሚመሰጠርባት ብቻ አይደለችም፣ ሃብት የሚሰበሰብባት፣ ገቢ የሚገኝባት ብርቅ ሥፍራም ናት እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ የላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ለማየት በሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በብዙ ስትጠቀም ኖራለች፣ አሁንም እየተጠቀመች ነው፡፡ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎችም ገቢያቸው እኒያ ቅዱስ ንጉሥ የሠሯቸውን አብያተክርስቲያናት ሊጎበኙ በሚመጡ እንግዶቿ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
እኒህ ደጋግ እንግዳ ተቀባይ ሰዎች ታዲያ ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ቀጥሎም በጦርነት ምክንያት ሰው የለመደው ቤታቸው ሰው ተርቦባቸው፣ ሰው የሚናፍቀው ዓይናቸው ሰው አጥቶባቸው ኖሯል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በመዳከሙ ክፉኛ ተጎድተው ኖረዋል፡፡
አካባቢው ከጦርነት ቀጣና ነጻ ከወጣ እና የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ እንደቀድሞውም ባይኾን የላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ እየኾነ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከጦርነቱ አስቀድሞ ስታስተናግዳቸው የነበሩ እንግዶችን ያክል እንግዶችን መቀበል አልቻለችም፡፡ በተለይ ደግሞ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል፡፡
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ ማንደፍሮ ታደሰ ላሊበላ የኢኮኖሚ መሠረቷ ከቱሪዝም የሚገኘው ሃብት መኾኑን ነግረውኛል፡፡ ከኮሮና ቫይረስና ከጦርነቱ አስቀድሞ በከተማዋ በዓመት ከ50 እስከ 60 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይጎበኟት ነበር፡፡ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተጎዳው ቱሪዝም ሳያገግም ጦርነት በመምጣቱ የጎብኝዎች እንቅስቃሴን ሙሉ ለሙሉ ማስቆሙንም ነው የነገሩኝ፡፡
ከጦርነቱ ማግሥት በ2015 ዓ.ም ተስፋ ሰጪ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ታይቷል፡፡ ከተማዋን በዘጠኝ ወራት ከ2 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ይጎበኟታል ብለው አቅደው ነበር። በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከእቅድ በላይ ከተማዋን ጎብኝተዋታል፤ የሀገር ውስጥ ጎብኚ ቁጥር ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በልደት ብቻ ሳይኾን በሌላው ጊዜም እየመጡ እየጎበኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በልደት ብቻ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በከተማዋ ከሦስት እስከ አምስት ቀን ቆይተውባታል ነው ያሉት፡፡
21 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሎ ተጠብቆ 3 ሺህ ጎብኚዎች ብቻ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ቁጥሩ ያሽቆለቆለ ቢኾንም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ተስፋ ሰጪ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ እና ከጦርነቱ አስቀድሞ 67 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከተማዋን ጎብኝተዋት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን በየጊዜው የሚፈጠሩ ወቅታዊ ኹኔታዎች ሊነቃቃ ያለውን ቱሪዝም እየጎዳው እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ የሚነሱ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች ቱሪስቶችን እያስቀራቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ቱሪስቶች ወደ ሥፍራው መጥተው ሰላም ካልተሰማቸው በሚጽፏቸው እና በሚያጋሯቸው ሃሳቦች ሌሎች እንዲቀሩ እንደሚያደርጉም ነግረውኛል፡፡
ያቺ ጎብኚዎች በብዛት የሚታዩባት ውብ ሥፍራ አሁን ላይ እዚህ ግባ የሚባል ጎብኚ የላትም፡፡ በልደት እና በጥምቀት ሰሞን ተስፋ የታየበት፣ ከዚያ ወዲህም ባሉት ጊዜያት መልካም እንቅስቃሴ የነበራት ከተማ በቅርቡ የጎብኚዎች ቁጥር ቀንሰውባታል ነው ያሉኝ፡፡
ሁሉም ከሰላም የሚገኘውን ትርፍ በማሰብ ለሰላም በመሥራት የቱሪዝም እንቀስቃሴውን ማነቃቃት ይገባልም ብለዋል፡፡ በተለይም የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ምንም አይነት ኮሽታ እንደማይፈልጉ ነው የነገሩኝ፡፡ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ቱሪዝሙ ወደ ነበረበት ይመለሳልም ነው ያሉት፡፡ ጥቂት ችግሮች ሲከሰቱ የሚያባብሱ አካላትም ቱሪዝሙን እየጎዱ ስለመኾናቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሰላም እና ለአንድነት በመሥራት ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን እንድታገኝ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ እና ሀገርን በመልካም መንገድ ለዓለም እንዲያስተዋውቁ መልካም መስተንግዶ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ላሊበላ ዓለምን ሁሉ የምትስብ፣ ሕዝብን ሁሉ የምታሳሳ፣ ታሪክን በታላቁ የምትነግር፣ ቀዳሚነትን የምትመሰክር ውብ ምድር ናት፡፡ ይህች አባት ውብ አድርጎ ያሳመራት ቅድስት ሥፍራ ጉርስም፣ ልብስም ናት፡፡ እዩዋት፣ እወቋት፣ ታሪኳን ንገሩላት፣ የምድሯን ሰላም ጠብቁላት፣ ያን ጊዜ በረከቷን ትሰጣለች፣ ኅብስቷን ታጎርሳለች፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!