ኢትዮጵያ ለ48ተኛ ጊዜ በተካሄደው የኢስላሚክ ዴቨሎፕመንት ባንክ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ተሳተፈች።

75

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለ48ተኛ ጊዜ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ለ4 ቀናት በተካሄደው የኢስላሚክ ዴቨሎፕመንት ባንክ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ በእንግድነት ተሳትፋለች።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግድነት የተጋበዘች መሆኑንና በሳዑዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ መገኘታቸው ተገልጿል።

ኢስላሚክ ዴቨሎፕመንት ባንክ 57 አባል ሀገራት ያሉት በዋናነት በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፍ የገንዘብ ተቋም መሆኑም ተመላክቷል።

ተቋሙ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ዓለም ባንክ ትልቅ የፋይናንስ አማራጭ ሲሆን በተለያዩ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በትምህርት በጤና እና ሁሉን አቀፍ እድገት ላይ በሚያተኩሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ለአባል ሀገራት ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል።

ተቋሙ አብዛኛውን የመሰረተ ልማት፣ የቢዝነስ፣ የሰብዓዊ እርዳታ እና የመሳሰሉትን ድጋፎች ለማድረግ አባልነትን እንደመስፈርት የሚጠይቅ በመሆኑ እና ኢትዮጵያም በዚሁ የፋይናንስ ተቋም አባል ባለመሆኗ ከባንኩ የምታገኘው ድጋፍ አነስተኛ እንዲሆን እንዳደረገው ነው የተጠቀሰው።

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር መሀመድ አል ጃስር፣ ከዚህ ቀደም ከአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ጎን ለጎን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በባንኩ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ተሳትፎ እንድታደርግ ጋብዘው የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው።

በጉባዔውም ቀጣይነት ያለው እድገት ስለሚረጋገጥበትና ላለፉት 30 ዓመታት ተግባራዊ እየሆነ ባለው የተረጋገጠ የልማት ግብ ላይ በተለይም በኮቪድ 19፣ በአየር ንብረት መዛባት እና በዓለማችን በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እያስከተሉ ያሉትን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጫና በተመለከተ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት ማድረጉም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ከዚህ አማራጭ የፋይናንስ ማዕቀፍ ተጠቃሚ እንድትሆን መንግሥት የሚገባውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማኀበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ሥርዓት ግንባታ እና አተገባበርን የተመለከተ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው።
Next articleየክልሉን ወቅታዊ ችግሮች እና የሕዝብን ጥያቄዎች መሠረት ያደረገ የአመራር ኮንፈረንስ ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል ብልጽግና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡